ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክከር ሂደቱ በአወያይነትና የአጀንዳ ሃሳብ በማቅረብ ጭምር ሴቶች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 21/2017(ኢዜአ):- በሀገራዊ ምክከር ሂደቱ በአወያይነትና የአጀንዳ ሃሳብ በማቅረብ ጭምር ሴቶች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን የሴቶች ማህበራት ሃላፊዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከግንቦት 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከሚገኙ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል።

በእስካሁኑ ሂደትም በዘጠኝ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ስራ አጠናቋል።

በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማካተት ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከዚህ አንፃር በምክክር ሂደቱ የሴቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል በማለት ኢዜአ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት እና የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበርን አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ዋና ዳይሬክተር ሳባ ገብረመድህን፤ የምክክሩን አስፈላጊነት በመረዳት የሴቶች ትብብርና ተሳትፎ የተጠናከረ መሆኑን አንስተዋል።

እንደ ሀገር የገጠሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከምንም በላይ መመካከር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት የላቀ ሚናውን እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሴቶች ጥምረት ለሴቶች ድምጽ በብሄራዊ ምክክር የሚል ጥምረት በመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጥምረቱም ሴቶችን በማወያየት የሚነሱ ሀሳቦችን በመሰብሰብ በማደራጀት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማስረከቡን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክከር ኮሚሽን በሚዘጋጁ መድረኮች በአወያይነትና የአጀንዳ ሃሳብ በማቅረብ ጭምር ሴቶች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት እናትአለም እንዳለ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው እድገት ችግሮችን በምክክር በመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚህም ሀገራዊ ምክክሩ መልካም እድል ይዞ የመጣ በመሆኑ ሁላችንም ልንጠቀምበት ይግባል ብለዋል።

በቀጣይም ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር በቅርበት የሚሰሩ መሆኑን ሃላፊዎቸቹ አረጋግጠዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም