የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወቅቱን የቴክኖሎጂ እውቀት በመላበስ ፕሮፌሽናል ሰራዊት የመገንባት ሂደቱን እያጠናከረ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የወቅቱን የቴክኖሎጂ እውቀት በመላበስ ፕሮፌሽናል ሰራዊት የመገንባት ሂደቱን እያጠናከረ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአየር ኃይል 89ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርኃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አየር ኃይል ያደረጋቸውን መልከ ብዙ የሪፎርም ተግባራት አድንቀዋል።

አየር ሃይል በተቋማዊ ግንባታ በአደረጃጀትና በአሰራር ራሱን እያሻሻለ የመጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሰው ሃይል ግንባታ ትኩረት በማድረግ የወቅቱን የቴክኖሎጂ እውቀት በመላበስ ፕሮፌሽናል ሰራዊት የመገንባት ሂደቱን እያጠናከረ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

አየር ኃይል በቴክኖሎጂ የበቃ የሰው ኃይል የማፍራትና ትጥቆችን የማደስ ሥራው ስኬታማ መሆኑንም ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ የሰራዊቱን መኖሪያ ቤት ችግር በመቅረፍ፣ አዳዲስ ትጥቅና የውጊያ መሰረተ ልማት በማሳደግ እንዲሁም ምቹና ውብ የሥራ አካባቢ መገንባቱንም አድንቀዋል።

በመሆኑም ዘመኑን የዋጀ ተቋም ለመንባት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አየር ኃይል በግብርናው መስክ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ሌላው ስኬት የተመዘገበበት መስክ መሆኑን ጠቁመዋል።

በወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውጤታማ መሆኑንና ከወዳጅ አገራት ጋር የሥልጠናና የዕውቀት ሽግግር መደረጉንም እንዲሁ።

አየር ኃይል ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ በአብዛኛው ግቡን እያሳካ መሆኑን ገልፀው ተቋሙ ወትሮ ዝግጁነቱን በማጠናከር ሕገ-መንግሥታዊ አደራውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የተጀመረውን ተቋም ግንባታ ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀው የዕለቱ ተመራቂዎችም የተቋሙ የተልዕኮ አፈፃፀም ስኬት አካል እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ አየር ኃይል የተመሰረተበት ሕዳር 20 ለአቪዬሽን ዘርፍ ልዩ ቀን በመሆኑ በቅጡ መዘከርና ማክበር ይገባናል ብለዋል።

የዘንድሮው 89ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲዘከር ቆይቶ ዛሬ መጠናቀቁን ገልፀዋል።

በዛሬው ዕለትም የአቪዬሺን ዘርፉን የሚያስቃኝ ዐውደ ርዕይ፣ የመሰረት ልማቶች ምረቃ እንዲሁም በተለያዩ ሙያዎች የሰለጠኑ የሰራዊት አባላት ምርቃት ሥነ-ሥርዓት መካሄዱን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ዘብ የሆነውን አየር ኃይል የመገንባቱ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አየር ኃይል የተጣለበትን ሀገራዊ ተልዕኮ ለማሳካት በውጊያ መሰረተ ልማትና በትጥቅ የተሟላ ተቋም ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

የዕለቱ ተመራቂዎችም የተሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና በሚገባ ያጠናቀቁና የተቋሙን ሥነ-ምግባር የተላበሱ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በቀጣይ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ሁሉ በብቃትና በታማኝነት በመወጣት ለአየር ሃይል የከፍታ ጉዞ አቅም እንዲሆኑ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም