ኢትዮጵያና ፈረንሳይ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ አጋርነታቸውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት ጋር ዛሬ ማምሻውን ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ውይይቱን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፤ ውይይቱ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ተናግረዋል።
የአውሮፓና የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂያን-ኖኤል ባሮት የኢትዮጵያ ጉብኝት ፈረንሳይ ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር የምትሰጠውን ትኩረት ያመላከተ ነው ብለዋል።
ፈረንሳይ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር ናት ያሉት ቃል አቀባዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ይህን ማስፋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ገልፀዋል።
በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በባህልና ቅርስ ጥበቃ፣ በኃይል አቅርቦት በአከባቢ ጥበቃና በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ማስፈን በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል።
ፈረንሳይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የአከባቢ ጥበቃ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር መደገፍ በምትችልበት ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረገችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ባለሃብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በውይይቱ ጥሪ መቅረቡን ተናግረዋል።