የአሪ ብሔረሰብ  ዘመን መለወጫ "ድሽታ ግና"  በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነትን የሚያጠናክሩ ናቸው 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦የአሪ ብሔረሰብ  ዘመን መለወጫ "ድሽታ ግና"  በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት የሚያጠናክሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱርዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) ተናገሩ። 

የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ "ድሽታ ግና" በአዲስ አበባ ብሔራዊ ቲያትር በድምቀት እየተከበረ ይገኛል። 

በመርኃ ግብሩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ "ድሽታ ግና" የሰላም፣ የይቅርታ፣ የመተሳሰብና የአንድነት ተምሳሌት በዓል መሆኑን ትውፊት ያስረዳል። 

ምስጋና፣ ፍቅር፣ መረዳዳት፣ ዕረቀ ሰላም፣ አብሮነትና ውበት የድሽታ ግና እሴቶችም ናቸው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱርዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ባህል ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ህይወትና ኑሮ መገለጫ ነው።

ብዙኃ ባህል ያላቸው አገራት ለተለያዩ ችግሮቻቸው የተለያዩ መፍትሄና ብልኃት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል። 

ኢትዮጵያዊ የብዙ ባህሎች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው እስከ አሁን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አለማግኘቷን አንስተዋል። 

በአገሪቱ የሚገኙ ብዙኃ ባህሎቻችን ማልማት፣ መጠበቅና የሚጠበቅባቸው አገልግሎት እንዲሰጡ የተጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ የሆነው "ድሽታ ግና" በውስጡ የያዛቸው እሴቶች ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታና አንድነት የሚያጠናክር ኃብት መሆኑን ገልጸዋል።  

በመሆኑም ባህላዊ እሴቶችን ለማልማት፣ ለመጠበቅና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመሩ ምቹ ዕድሎች መኖራቸው ጠቅሰው ተጠናክሮ ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም