በክልሉ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶች ይጠናከራሉ
ሆሳዕና ፤ህዳር 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረጉ ባሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች የተመዘገቡ ውጤቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ ።
ቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርዓተ ምግብ አገልግሎትን በተመለከተ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ እንደተናገሩት በሩብ ዓመቱ ከ85 ነጥብ 5 በመቶ በላይ የሚሆኑ እናቶች በጤና ተቋማት በሰለጠኑ ባለሙያዎች የወሊድ አገልግሎት አግኝተዋል።
ይህም በእናቶች ላይ በተሰራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክንያት የተገኘ መሆኑን ገልፀው በየጊዜው ከፍተኛ መሻሻል እየታየበት መሆኑን አውስተዋል።
በክልሉ ከአንድ አመት በታች ላሉ ህጻናት የሚሰጥ ክትባትን በማስመልከት በሩብ ዓመቱ መቶ በመቶ መከናወኑን አስረድተዋል።
በአፍላ ወጣቶችና የቤተሰብ እቅድ ላይ እድሜያቸው ለአቅመ ሄዋን የደረሱ ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
የስርዓተ ምግብ ጤና አገልግሎትን በማጠናከር ረገድም የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለዚህም በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በመለየትና ዘላቂ መፍትሄን በመስጠት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በቢሮው የእናቶችና ህፃናት ጤናና ስርዓተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሌጂሶ በበኩላቸው የረጅም ጊዜ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የእናቶችን ሞት በ40 በመቶ ለመቀነስ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አንስተው የእናቶች የቅድመ ወሊድና በህፃናት ክትባት አገልግሎት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን አስረድተዋል።
በአንጻሩም በስርዓት ምግብ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የእናቶችና ህፃናትን የጤና እክል ለመከላከል የተሰራው ስራ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም በሩብ ዓመቱ የተስተዋሉ ደካማ ጎኖችን ለማስተካከል ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ በዞኑ የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚያስችል ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ድረስ ያለውን ሂደት ጤናማ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የወላድ እናቶች ማረፊያን በማመቻቸት፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በመመደብና የህክምና ግብዓትን በማሟላት የእናቶች ሞትን ለመቀነስ የሚያስችል ስራ የተሰራ ሲሆን ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በተቀናጀ መንገድ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን ጤና መምሪያ ኃላፊዎችና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል።