የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ቀንን ስናከብር ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት

ደብረ ብርሀን ፤ ህዳር 20/ 2017 (ኢዜአ )፤-  የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ቀንን ስናከብር ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንዳለበት የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አስታወቀ። 

 ’’አገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት’’  በሚል መሪ ሀሳብ  19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መንግስቱ ቤተ በበዓሉ ላይ እንደገለጹት፤ በዓሉን ስናከብር የገጠሙን ፈተናዎችን  በማለፍና ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር መሆን አለበት።

ቀኑ ዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብቶቻቸውን ያረጋገጠው ህገ መንግስት የጸደቀበት ዕለትን በመዘከር ለአሁናዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በመነሳሳት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በተጨማሪም የአብሮነታችንና የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን ለማጠናከር የሚያስችሉ የቋንቋ፣ የባህልና ወግ እሴቶቻችንን ለማዳበር በሚያስችል መልኩ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

የዘንድሮውን በዓል ስናከብርም የተጀመረውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል በአንድነት በመሰለፍ መሆኑንም አስረድተዋል።

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከልም አቶ አሻግሬ በየነ እንደገለጹት፤ በዓሉ አንድነትንና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው።

ሌላዋ ተሳታፊ ወይዘሮ  ላቀች ንጉሴ በበኩላቸው፤ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ የዜጎችን መፈቃቀርና የባህል ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ህገ መንግስቱም ሴቶች በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና ማህበራዊ ዘርፉ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ መሆኑን ጠቁመው፤ "ያጋጠሙ ፈተናዎችን  በቁርጠኝነት ለማለፍ  የምንመክርበት ነው" ብለዋል። 

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ዓይናለም ተክለሩፋኤል እንደገለጹት፤ ቀኑ ሲከበር አንድነታችንን በማጠናከርና ክፍተቶች እንዲታረሙ  በመወያየት ሊሆን እንደሚገባም አንስተዋል።  

በተለያዩ ዝግጅቶች በተከበረው በዓል ላይም የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም