የበዓሉን አጋጣሚ በመጠቀም በቱሪዝም ልማት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የበዓሉን አጋጣሚ በመጠቀም በቱሪዝም ልማት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገለፀ
አክሱም ፤ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፥ የአክሱም ፅዮን ማርያም የንግስ በዓልን አጋጣሚ በመጠቀም በቱሪዝም ልማት የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለፀ።
የአክሱም ጽዮን ማሪያም የንግስ በዓልን አጋጣሚ ለቱሪዝም ልማት በማዋል የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለመ ሲምፖዚየምና ዓውደ ርዕይ ዛሬ በአክሱም ተካሄዷል።
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ብርሃነ በሲምፖዝየሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፣ መሰል ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላትን ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው በመሆናቸው አጋጣሚውን ለቱሪዝም ልማት መጠቀም ይገባል።
በየዓመቱ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ምዕመናን እና የተለያዩ አገራት ጎብኚዎች የሚታደሙበት በዓል መሆኑን ጠቁመው፤ አጋጣሚውን ለቱሪዝም ልማት በማዋል የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
በዓሉ በአክሱምና አካባቢው ተዳክሞ የቆየውን የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥርም የበዓሉን ድባብ በመጠቀም ወደ ነበረበት ለመመለስ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች፣ የግልና የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው ብለዋል።
"ቅርሶቻችንን መጠበቅና መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ከፍ ብለው እንዲታዩ ማህበረሰቡም በንቃት የድርሻውን ሊወጣ ይገባል" ያሉት ፕሬዚዳቡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በቅንጅት የመስራት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
የአክሱም ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመድህን ፍፁምብርሃን በበኩላቸው፣ የቱሪዝም ልማት የቅድሚያ ትኩረት የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን አንስተዋል።
''በትግራይ ክልል የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ ነገ ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም በሚከበረው የጽዮን ማሪያም ንግስ በዓል ላይ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል'' ያሉት ኃላፊው፣ ''የሚፈጠረውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከእኛ ይጠበቃል'' ብለዋል።
ሰላምና ቱሪዝም የማይነጣጠሉ ክስተቶች ናቸው ያሉት አቶ ገብረመድህን፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ለሚመጡ እንግዶች በከተማው ውስጥ ያሉ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎችን የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ተሳታፊዎች የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የቱሪዝም ዘርፎችን በመለየት በቅንጅት ለመስራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
ዛሬ በአክሱም ከተማ በተዘጋጀው ዓውደ ርዕይ ላይም የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት እና ቅርፃ ቅርፅ ለገበያ ቀርበዋል።
ስምፓዚየሙና አውደ ርዕዩ የተዘጋጀው በአክሱም ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት፣ በአክሱም ዩኒቨርሲቲና በአክሱም ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት መሆኑም ተመልክቷል።