በክልሉ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ ይቀጥላል-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) 

ባህር ዳር ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በምግብ ራስን ለመቻል እየተተገበረ የሚገኘው የበጋ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) አስታወቁ።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማስጀመሪያ ንቅናቄና የትራክተር ርክክብ ስነ-ስርዓት በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ተካሄዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጠናክሮ ይቀጥላል።


 

ባለፉት ዓመታት የተጀመረው የበጋ ስንዴ ልማት ስራ በየዓመቱ እያደገና የአርሶ አደሩ አጀንዳ እየሆነ በመምጣቱ ከውጭ የሚገባውን ስንዴ እንደ ሀገር ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በበጋ ወቅት ስንዴ ማልማት ሐሳቡ እንዳልነበረ ጠቅሰው፤ ይህም ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነው ያልተቋረጠ ጥረት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችሉ የትራክተር ቴክኖሎጂዎች፣ የምርጥ ዘርና የግብዓት አቅርቦትን የተሳለጠ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተተገበረ ነው።

ከዚህ ውስጥ 254 ሺህ ሄክታሩ በበጋ መስኖ ስንዴ ለማልማት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ልማቱን ለማሳለጥም ባለፈውና በዚህ ዓመት ከ10 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመትም ለመስኖና ለመጭው የመኸር ወቅት የሚውል ማዳበሪያና የምርጥ ዘር በበቂ ሁኔታ የማቅረቡ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ግብርናውን ለማዘመንና ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት እስካሁን በተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት 200 የሚጠጉ የእርሻ ትራክተሮች ተሰራጭተው አርሶ አደሩን እያገዙ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በዞኑ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ24 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የሰሜን ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሰፋ ጥላሁን ናቸው።


 

ከዚህ ውስጥ 19 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ780 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም በ82 ሚሊዮን ብር የተገዙ 13 ትራክተሮች ለአደሮች ርክክብ መካሄዱን ተናግረዋል።

በበጋ መስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመሪያና የትራክተር ርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይም የክልሉና የሰሜን ጎጃም ዞን አመራሮች፣ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም