የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመኑን የዋጀ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነው-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመኑን የዋጀ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ የተደረገው ጥረት ውጤታማ ነው-ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘመኑን የዋጀ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአየር ኃይል 89ኛ ዓመት ክብረ በዓል ማጠቃለያ መርኃ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፦አየር ኃይል ያደረጋቸውን መልከ ብዙ የሪፎም ተግባራት አድንቀዋል።
ዘመኑን የዋጀ ተቋም ለመንባት የተደረገው ጥረት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፥ ፕሮፌሽናል ሰራዊት እየተገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
አየር ኃይል በቴክኖሎጂ የበቃ የሰው ኃይል የማፍራትና ትጥቆችን የማደስ ሥራው ስኬታማ መሆኑንም ገልጸዋል።
አየር ኃይሉ የሰራዊቱ መኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ፣አዳዲስ ትጥቅና የውጊያ መሰረተ ልማት የማሳደግ ሥራው እንዲሁም ምቹና ውብ የሥራ አካባቢ መገንባቱንም አድንቀዋል።
አየር ኃይል በግብርናው መስክ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ሌላው ስኬት የተመዘገበበት መስክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወታደራዊ ዲፕሎማሲ ውጤታማ መሆኑንና ከወዳጅ አገራት ጋር የሥልጠና የዕውቀት ሽግግር መደረጉንም እንዲሁ።
አየር ኃይል ኢትዮጵያን የሚመጥን ተቋም ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ በአብዛኛው ግቡን እያሳካ መሆኑን ገልፀው፥ተቋሙ ወትሮ ዝግጁነቱን የማጠናከር እንዲሁም ሕገ-መንግሥታዊ አደራውን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የተጀመረውን ተቋሞ ግንባታ ማጠናከር እንደሚገባ ገልፀው፥የዕለቱ ተመራቂዎችም የተቋሙ የተልዕኮ አፈፃፀም ስኬት አካል እንዲሆኑ አሳስበዋል።