በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በተሳለጠ መንገድ እንደሚተገበር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በተሳለጠ መንገድ እንደሚተገበር ተገለጸ
ሀዋሳ፤ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦በግብርናው ዘርፍ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታን በተሳለጠና በተናበበ መንገድ ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው የሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በግብርናው ዘርፍ ያሉ አቅሞችና ጸጋዎችን ለይቶ የማልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲና የተለያዩ ዕቅዶች መነደፋቸውን ጠቅሰው፣ ፖሊሲና ዕቅዶቹን በተሳለጠ መንገድ ለማሳካት በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተለይ ግብርናውን ለማዘመንና በዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ፍኖተ ካርታው በተናበበና በተሳለጠ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
"በዚህ ረገድ እስካሁን ለአራት ክልሎች የግብርና ሽግግር ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ተገብቷል" ያሉት ሚኒስትሩ፣ ዛሬም ለሲዳማ ክልል የተሰናዳው ፍኖተ ካርታ ይፋ ተደርጓል ብለዋል።
"ፍኖተ ካርታው ያሉንን ጸጋዎችና አቅሞች መለየት ብቻ ሳይሆን እንዳንጠቀማቸው ያደረጉንን ተግዳሮቶች የለየና የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በመቅረጽ ወደ ሥራ የሚገባበትን አቅጣጫ ያመላከተ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ለክልሉ የተዘጋጀው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ነው።
"በተለይ በክልሉ ያለውን እምቅ አቅም አውቆ ለማልማትና ወደ ሀብት ለመቀየር መነሳሳትና አቅም የፈጠረ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በፍኖተ ካርታው ዝግጅት ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ኑሮው በግብርና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ደስታ፣ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህንን ሥራ ይበልጥ ለማስፋፋት፣ የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና በዘርፉ አመርቂ ተግባር ለማከናወን ፍኖተ ካርታው ተጨማሪ ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ አውደ ጥናት ላይ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴን ጨምሮ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።