የፀሐይ-2 አውሮፕላን መሃንዲሶችና ቴክኒሻኖች አስተባባሪው ኮሎኔል መመኪያ መዝገቡ አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ-2 አውሮፕላን መሃንዲሶችና ቴክኒሻኖች አስተባባሪው ኮሎኔል መመኪያ መዝገቡ አንደበት
በሰውም ሆነ ያለሰው መብረር የምትችለው የፀሐይ-2 አውሮፕላን መሃንዲሶችና ቴክኒሻኖች አስተባባሪ ከሆኑት ኮሎኔል መመኪያ መዝገቡ አንደበት።
በኢትዮጵያ አየር ኃይል ፀሐይ-2ን የሰሩት የአየር ኃይል መኃንዲሶችና ቴክኒሻኖች አስተባባሪ ኮሎኔል መመኪያ መዝገቡ ስለ ስራውና አጠቃላይ የአውሮፕላኗን አገልግሎት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በአየር ኃይል የከባድ ጥገና ማዕከል የሰው አልባ አውሮፕላን ጥገናና ማምረቻ የትስስርና ሙከራ ኃላፊም በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።
ኮሎኔል መመኪያ ከ89 ዓመታት በኋላ ፀሐይ-2 አውሮፕላንን በራስ ሙያተኞች በመስራት የተሳካ አሻራቸውን በማኖራቸው ደስታቸው ወደር የሌለው መሆኑን ይናገራሉ።
አባቶች በዘመኑ ቴክኖሎጂ ሀገር አሻግረዋል፣ እኛም ዕውቀትና ጊዜ ተጠቅመን በዘመኑ ቴክኖሎጂ ለሀገር የሚበጅ ቁምነገር በመስራት አዲስ የታሪክ አሻራ በማኖራችን ታላቅ ኩራት ተሰምቶኛል ይላሉ።
በኢትዮጵያ አየር ሃይል የተሰራችው ፀሐይ - 2 አውሮፕላን አገልግሎቷ ሁለገብ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
አውሮፕላኗ ዘመናዊና የረቀቀ ቴክኖሎጂ የተገጠመላት ሲሆን ለልምምድ፣ለውጊያ፣ለአየር ቅኝትም ሆነ ሌሎችም ሁለገብ አገልግሎቶች የምትውል መሆኗን ገልጸዋል።
የፀሐይ -2 ሌላኛው ልዩ መገለጫ ደግሞ በአብራሪም ሆነ ያለአብራሪ ወይም እንደ ድሮን መብረር የምትችል መሆኗን ኮሎኔል መመኪያ ጠቁመዋል።
የፀሐይ-2 አውሮፕላን ሥራ ላይ ልምድ ያላቸው የቴክኒክ ባለሙያዎችና መሀንዲሶች የተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል።
በስራው ሂደት የታየውም የኢትዮጵያ አየር ሃይል ያለውን ዕቅም ወደ እሴት የለወጠባት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአየር ኃይሉ ባለሙያዎች የተሰራችው ፀሐይ-2 የኢትዮጵያዊያን የመስራት አቅም የታየባት እንዲሁም የዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር የተደረገባት ስለመሆኑም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን አየር ኃይል የመዘመንና የማድረግ አቅም ያሳየና ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን መሪ መሆኑን በተግባር የገለጠበት ነው ብለዋል።
የአየር ኃይል የፈጠራና ቴክኖሎጂ ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አንስተው፥ የመፍጠር አቅም ያላቸው ሁሉ ከተቋሙ ጋር በመስራት ለሀገር የሚተርፍ አሻራ እንዲያሳርፉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ''ጸሐይ-2'' የተሰኘችና በአየር ኃይሉ የተሰራች አውሮፕላን ለበረራ ብቁ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለፃቸው ይታወቃል።
ይህም በ2030 በአፍሪካ ስመጥር አየር ኃይል ለመሆን የያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው ሲሉም ተናግረዋል።