የአፋር ህዝብ ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳደግና ለማበልፀግ ያደረገው ትግል ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ህዝብ ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳደግና ለማበልፀግ ያደረገው ትግል ውጤት ማምጣቱ ተገለጸ
ሰመራ ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦የአፋር ህዝብ ቋንቋውንና ባህሉን ለማሳደግና ለማበልፀግ ያደረገው ትግል ውጤት ያመጣበት መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ መሐመድ ተናገሩ።
"አገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያና ሶማሌ ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈ ጉባዔዎች በተገኙበት 19ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሰመራ ተከብሯል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ መሐመድ እንደገለጹት፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንን የአፋር ህዝብ እንደ ሌሎች ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ቋንቋው እና ባህሉን በእኩልነት ለመጠቀም አስችሎታል።
ዕለቱ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ የሆነው ህገ መንግስት የፀደቀበት ቀን መሆኑን አስታውሰዋል።
"ይህም ህብረ ብሄራዊ አንድነታችንን በማጎልበት ለሌሎች አገሮች ተምሳሌት እየሆን የመጣንበት ነው" ብለዋል።
ላለፉት ዓመታት የአፋር መሬት ለልማት ሳይውል መቆየቱን ጠቅሰው፤ በቅርብ ዓመታት ሰብሎች፣ አዝዕርት፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች በማልማት ከፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ መቅረቡን አብራርተዋል።
በመድረኩ ላይ "የእንኳን ደህና መጣችሁ" ንግግር ያደረጉት የአፋር ክልል አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል እንደገለጹት፤ በዓሉን ማክበር የርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር አስችሏል።
ቀኑን "ዛሬ ከሌሎች ጋር በአንድነት በህብር አክብረናል" ብለዋል።