በመቀሌ በቅርቡ ወደ ገበያ የገቡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተፈላጊነት እየጨመረ መሆኑ ተገለፀ

መቀሌ ፤ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦  በመቀለ በቅርቡ ወደ ገበያ የገቡት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በተጠቃሚዎች ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱን የከተማዋ የተሽከርካሪ አቅራቢዎችና ተጠቃሚዎች ገለጹ።

የተሽከርካሪዎቹ የአየርና የድምፅ ብክለትን የመከላከል ብቃት ገበያ ላይ ተመራጭ እየሆኑ ለመምጣታቸው ምክንያት መሆኑንም የተሽከርካሪዎቹ አቅራቢዎች አመልክተዋል። 

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን በበኩሉ፣ ተሽከሪካሪዎቹ የሚጠቀሙት ቴክኖሎጂ የአየርና የድምፅ ብክለትን የሚቀንሱ በመሆናቸው በመንግስት ይብረታታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪን አስፈላጊነት አስመልከተው ባስተላለፉት መልዕክት ቴክኖሎጂው ለኢትዮጵያ በብዙ መልኩ እንደሚጠቅማት መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ የማምረት አቅም ስላላት ‘’ከወዲሁ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ማምረት ከጀመርን የዛሬ አምስት እና አስር ዓመት የምንመኛትን፣ የበለጸገች አገር ለማየት የሚቻል መሆኑን አመላካች ነው።’’ ማለታቸውም እንዲሁ። 

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተሽከርካሪዎቹ ወደ አገልግሎት መግባት በአየር ብክለት ሳቢያ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በእጅጉ እንደሚቀንስ መግለጻቸውም ይታወሳል።

በመቀሌ በተሽከርካሪ ሽያጭ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ መሀሪ ዮሴፍ እንደገለጹት፣ የተሽከርካሪዎቹ ተፈላጊነት ሊጨምር የቻለው ከነዳጅ ጋር የተያያዙ ወጪዎችን በማስቀረታቸውና ጭስ አልባ በመሆናቸው ነው'' ብለዋል።

ስለሆነም በአካባቢ ላይ ምንም ዓይነት ብክለት እንደማያስከትሉም አቶ መሃሪ ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን ፍላጎት በማጥናት ካለፈው ሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ በማስመጣት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ አቶ ሀዱሽ አርዓያ ናቸው። 

ድርጅታቸው ለተጠቃሚዎች ተሽከርካሪዎቹን ቻርጅ በማድረግ ረገድ እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል። 

መሪጌታ ይሄይስ ከበደ ሌላው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ተሽከርካሪ ተጠቃሚ እንደሆኑ በመግለጽ፣ የነዳጅና ሌሎች ተዛማጅ ወጪዎችን የሚያስቀርላቸው እንደሆነም ገልጸዋል። 

አንዴ ቻርጅ ካደረጉት በኋላ ለብዙ ቀናት እንደሚጠቀሙበት የተናገሩት መሪጌታ ይሄይስ፤ "በዋነኛነት በነዳጅ ጉዳይ ከመጨነቅ እንዳዳናቸውና ብክለት አልባ በመሆኑ እንድመርጠው አድርጎኛል'' ብለዋል። 

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የአየር ንብረት ለውጥ ክትትልና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ህሉፍ ሀጎስ  እንደገለጹት፤ መንግስት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ መገንባትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። 

ባለሀብቶች ብክለት አልባ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ በማቅረብ ረገድ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ እንደ ክልል የሚደገፍና ሊበረታታ የሚገባው ጉዳይ መሆኑንም አክለዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም