ህገ መንግሥቱ የአገሪቷን ብዝሃ ባህልና ህብረ ብሔራዊነትን እውነት ፊት ለፊት ያወጣ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ህገ መንግሥቱ የአገሪቷን ብዝሃ ባህልና ህብረ ብሔራዊነትን እውነት ፊት ለፊት ያወጣ መሆኑ ተገለጸ
ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ለብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መከበር መሠረት የሆነው ህገ መንግሥት የኢትዮጵያን ብዝሃ ባህልና ህብረ ብሔራዊነትን እውነት ፊትለፊት ያወጣ መሆኑ ተገለጸ።
39ኛው የ"ጉሚ በለል " የውይይት መድረክ "አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ዛሬ ተካሂዷል።
በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤትና በክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አዘጋጅነት የተሰናዳው መድረክ በክልሉ ደረጃ የሚከበረውን 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ምክንያት በማድረግ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ እሸቱ ሲርኔሳ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ጥንታዊ የአፍሪካ ቀንድ ታላቅ አገርና ረጅም የአገረ መንግሥት ግንባታ ያላት ናት።
የብዙ ጀግኖች፣ ብዝሃ ማንነትና ባህል ያላት አገር እንደሆነች ጠቅሰው፤ ሆኖም በነጠላ ትርክት የተነሳ የህዝቦቿ ብዝሃነት ተገቢውን ክብር ሳያገኙ መቆየታቸውን አንስተዋል።
በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መራራ ትግል እና መስዋዕትነት በመጣው ለውጥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብቱን ያጎናጸፈው የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት መጽደቁን ያነሱት አቶ እሸቱ፤ የኢትዮጵያን ብዝሃ ባህልና ህብረ ብሔራዊነት ሀቅ ይፋ ያወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ህብረ ብሔራዊነትን ያከበረው ህገ መንግሥቱ በመፈቃቀርና በመተማመን ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲጠናከር በማስቻሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ ማስተዳደርና ለዴሞክራሲ ግንባታ ዋስትና የሰጠ በመሆኑም ጭምር ዕለቱ በየዓመቱ እየተከበረ መሆኑን አንስተዋል።
በጨፌ ኦሮሚያ የበጀትና የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገመቹ አራርሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ታሪካዊና በአገሪቷ ረጅም የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ልዩ ትርጉም የሚሰጠው ነው።
እለቱን አስመልክቶ "አገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል ርዕስ መነሻ የውይይት ጽሁፍ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁር በሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዘላለም ተስፋዬ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበታል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከሸገር ከተማ አስተዳደር የመጣው ወጣት ተስፋዬ ቤኩማ እንዳለው ፤ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ማክበሩ ለአንድነት፣ ለጋራ እድገትና ለወንድማማችነት መጠናከር ያለው ፋይዳ የጎላ ነው።