በስነምግብ ይዘታቸው የበለጸጉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በስነምግብ ይዘታቸው የበለጸጉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል

ሀዋሳ ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ ድርቅና በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡና በስነምግብ ይዘታቸው የበለጸጉ የስኳር ድንች ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ ምርታማነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው አርሶ አደሮችም ከምርምር ማዕከሉ ያገኙትን ብርቱካናማ ስኳር ድንች በማምረት ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በምርምር ያገኛቸውን ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና የቫይታሚን "ኤ" ይዘት ያላቸውን "ካቦዴና አላሞራ" የተሰኙ ብርቱካናማ የስኳር ድንች ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች አስተዋውቋል።
በኢንስቲትዩቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ምርምር ዳይሬክተር አዲሱ በዛብህ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ በ23 ማዕከላት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት የሚያግዙ የምርምር ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
ድርቅና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙና በሥነ ምግብ ይዘታቸው ከበለጸጉ የሥራስር ምርቶች መካከል ስኳር ድንች ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ስኳር ድንቹ በትንሽ መሬት ከፍተኛ ምርት መስጠት እንደሚችል ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት ከ10 በላይ የስኳር ድንች ዝርያዎችን የማፍለቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ ጥቅም ላይ የዋሉ ዝርያዎች በቫይታሚን "ኤ" ይዘታቸው የበለጸጉ እንደሆኑም አስረድተዋል።
በኢንስትቱዩቱ የወንዶ ገነት ምርምር ማዕከል የሥራስር ሰብሎች ተመራማሪ አቶ ዳምጠው አብወይ በበኩላቸው ፣ ውጤታማነቱ በማዕከሉ ተረጋግጦ ለተጠቃሚዎች የተላለፈው ብርቱካናማ ስኳር ድንች በቫይታሚን "ኤ" ንጥረ ነገር የበለጸገ መሆኑን ተናግረዋል ።
ዝርያው በምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰት የመቀንጨር ችግርን ለመከላከል የሚያስችሉ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።
ስኳር ድንቹን በማልማት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት ስኳር ድንች ከነባሩ ዝርያ ጋር ሲነጻጸር ቶሎ ከመድረስ ባለፈ ብዙ ምርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በእዚህም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ የስኳር ድንች ዝርያው የመሬት ለምነትና እርጥበትን ለመጠበቅ እያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ምርቱ ፈጥኖ የሚደርስ ከመሆኑ በላይ ብዙ ውሃ እንደማይፈልግ ገልጸው፣ ምርቱ ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ ድንች ምርምር ተቋም የኢትዮጵያ ቢሮ ተጠሪ ሰጠኝ ገበየሁ (ዶ/ር) በበኩላቸው ስኳር ድንች በአነስተኛ ማሳ ከፍተኛ ምርት መስጠቱና የስነ ምግብ ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል ብለዋል።
ድርቅን ተቋቁሞ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለምርት የሚደርስና ስነምግብን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የስኳር ድንች ዝርያዎችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመርሀግብሩ የስኳር ድንች ዝርያውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ከስኳር ድንች የተዘጋጁ እንጀራና የተለያዩ ምግቦች ለእይታ ቀርበዋል።