ቀጥታ፡

የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ ቢሆንም የመከላከል ስራን ማጠናከር ያስፈልጋል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ ቢሆንም የመከላከልና የመቆጣጠር ስራን ማጠናከር እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የዓለም ኤድስ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 22/2017 ዓ.ም እንደሚከበርም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ መንግስት ኤች አይ ቪ/ኤድስን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

ኤች አይ ቪ/ኤድስ በአምራች የሰው ኃይል ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅእኖ ለመቅረፍ ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን አስቀድመው ከበሽታው መከላከል እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና ህብረተሰቡ የጤና ምርመራ ባህልን እንዲያዳብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ቫይረሱ የተገኘባቸው ዜጎች በጤና ተቋማት ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል።

የዘንድሮም የዓለም የኤድስ ቀን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የህክምና አገልግሎት በተገቢው ለዜጎች ተደራሽ ማድረግ ላይ ባተኮረ መልኩ እንደሚከበር ገልፀዋል።

እንደ ሀገር የበሽታው ስርጭት ምጣኔ ከፍተኛ ከነበረበት ወደ 0 ነጥብ 87 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የስርጭት መጠኑ የቀነሰው ተለዋዋጭ ስትራቴጂዎችን በመተግበርና ሁሉንም ማህበረሰብ አካታች የሆነ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች በመከናወናቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ የበሽታው ስርጭት አሁንም በማህበረሰቡ ላይ የጤና፣ የልማት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ችግሮችን እያስከተለ ነው ብለዋል።

ከበሽታው አሳሳቢነት አንፃር አሁንም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሽታ ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የመከላከል ስራ ለማከናወን ኢንስቲትዩቱ ቅኝትና ጥናት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም