በሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት እየተደረገ ነው
ሀዋሳ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ባዘጋጀው የሲዳማ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ ላይ ያተኮረ ውይይት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ኢንስቲትዩቱ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለክልሉ ያዘጋጀው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታን ዛሬ ለክልሉ መንግስት እንደሚያስረክብ ተመላክቷል።
በግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ አውደ ጥናት መድረክ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ(ዶ/ር) እና ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ እንደተገለጸው ፍኖተ ካርታው የተዘጋጀው የክልሉን የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ሲሆን ለቀጣይ አስር ዓመት ተግባራዊ የሚደረግ ነው ተብሏል።
በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ፍኖተ-ካርታው የግብርና እድገት ትንሳኤ አብሳሪ ነው ብለዋል።
በሲዳማ ክልል የምግብ ዋስትናን እና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሳለጥም ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቁመው፣ ፍኖተ ካርታውን ላዘጋጁ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው ፍኖተ-ካርታውን በብቃት መተግበር ያለውን ጠቀሜታ ገልጸው፤ ለተግባራዊነቱ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ማዕከላት፣ ከግሉ ዘርፍ እና ከልማት አጋሮች የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ አሳስበዋል።
የፍኖተ-ካርታው ባለቤትነት በክልሉ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የተለያዩ ሴክተሮች መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ፍኖተ- ካርታው በሰብል እና በተፈጥሮ ሀብት ንዑስ ዘርፎች ላይ ያተኮረ መሆኑንም አመላክተዋል።
የፍኖተ ካርታ ዝግጅቱ አሁን ያሉትን ፀጋዎችና አቅም በመለየት የበለጠ ለማልማት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ያካተተ ነው።
የአውደ ጥናቱ ዓላማ በጋራና በቅንጅት ፍኖተ-ካርታውን ወደ ተግባር ለመቀየር የጋራ አቅጣጫ ለመያዝ መሆኑን ገልጸው፣ ሚኒስቴሩ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሸን ኢንስቲትዩት እስካሁን ድረስ ለአፋር፣ ጋምቤላ፣ ለሶማሌ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የግብርና ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅቶ ማስረከቡን አስታውሰዋል።
ዛሬም ለሲዳማ ክልል ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ የሚያስረክብ ሲሆን በቀጣይም የቤንሻንጉል ክልልን ፍኖተ ካርታ ይፋ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።