ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበትን 89ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበትን 89ኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው።

በመርሃ ግብሩ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዋጂ፣ የሰራዊቱ መኮንኖች፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይሎች አዛዦች፣ ወታደራዊ አታሼዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

ሕዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም የተመሰረተው እና የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት በማስከበር የደማቅ አኩሪ ገድል ባለቤቱ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ ዓመቱን "የተከበረች ሀገር የማይደፈር አየር ኃይል" በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች እየዘከረ ነው።

በሌላ በኩል ክብረ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በአየር ሃይሉ ግቢ ውስጥ የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይም በፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በይፋ ተከፍቷል።

በዐውደ ርዕዩ በአየር ኃይሉ ተሰርታ ለበረራ ዝግጁ የሆነችውን "ፀሐይ 2" አውሮፕላንን ጨምሮ በአየር ኃይል፣ በመከላከያ ዩኒቨርሲቲ፣ በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ስራዎችን የሚያስቃኙ የአቪዬሽን እና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ትጥቆች ለዕይታ ቀርበዋል።

በእለቱ በስልጠና ላይ የቆዩ የአየር ኃይል አብራሪዎች፣ ዕጩ መኮንኖችና የአቪዬሽን ጥገና ባለሙያዎች የሚመረቁ ይሆናል።

የአብራሪዎችና የሌሎች የሰራዊቱ አባላት መኖሪያ ቤቶች፣ የመመገቢያ አዳራሽ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገዶችና ልዩ ልዩ መሰረተ ልማት ስራዎች በክብር እንግዶች ተመርቀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ከማስከበር ባሻገር ለአፍሪካ ሀገራት አየር ክልል በመጠበቅና የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በማሰልጠን ደማቅ አሻራ ያኖረ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም