ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቂት ወራት ውስጥ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን እያየን ነው- በኢትዮጵያ የዴንማርክ ምክትል የሚሲዮን መሪ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቂት ወራት ውስጥ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን እያየን ነው ሲሉ በኢትዮጵያ የዴንማርክ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሰባስቲያን ሉካስ ባች ተናገሩ።

ለረጅም ዘመናት የዘለቀው የኢትዮ- ዴንማርክ የሁለትዮሽ ግንኙነትም በልማትና በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የዴንማርክ ምክትል የሚሲዮን መሪ ሰባስቲያን ሉካስ ባች፤ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ሁለቱ አገራት የአየር ፀባይ ለውጥን ለመከላከል፣ ለአየር ፀባይ ለውጥ የማይበገርና በቀጣይ የሚፈጠሩ የአየር ፀባይ ለውጦችን የሚቋቋም ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በጋራ እየሰሩ ነው።

በበርካታ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን በመጥቀስ ለማሳያነት የግብርና እና የኃይል ዘርፉን ጠቅሰዋል፡፡

የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተከትሎ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትም አስደናቂና በማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በጥቂት ወራት ውስጥ አስደናቂ ስኬት እያስመዘገበ መሆኑን እያየን ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ግብርናን በመከተል፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና በተለይም የኃይል ተደራሽነትን በማስፋት ጥሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም አንስተዋል።

በዚህ ረገድ ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የብዙዎችን ህይወት ለመለወጥ እያገዘ ያለውን የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ምርታማ ለማድረግ የዴንማርክ ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም