ቀጥታ፡

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በኢነርጂ ልማት እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልግ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ):- የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በኢነርጂ እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች ላይ በጋራ የመስራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር ) የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት እና የቦርድ ሊቀመንበር ጂን ሊኩንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።


 

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽንና ንጽህና አጠበበቅ፣ በውሃ ሀብት አስተዳደርና በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ላይ ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በዘርፉ ጥሩ ልምድና ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ኮይሻ ያሉ የውሃ ሃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ ጥሩ ተሞክሮ እንዳለም አንስተዋል።

ከዚህ አኳያ የኢንቨስትመንት ባንኩ ለኃይል ማመንጫ መሰረተ ልማቶች ውጤታማነትና የህብረተሰብ አገልግሎት ተደራሽነት የሚያስፈልገውን ዘመናዊ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት እየተደረገ ላለው ጥረት እና ኢትዮጵያ ላላት ከፍተኛ ኃይል የማመንጨት አቅም ባንኩ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠይቋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ(ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ የመብራት አገልግሎት ተደራሽ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ ትልቅ መሰረተ ልማት መዘርጋት የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት እና የቦርዱ ሊቀመንበር ጂን ሊኩን በውሃና ኢኒርጂ ሚኒስቴር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አድንቀዋል።

ባንኩ ከሚኒስቴሩ የኃይል አቅርቦትና የአየር ንብረት ለውጥ መቀነስን ጨምሮ ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ በትብብር መስራት እንደሚፈልግ መግለጻቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) እና የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ከእስያ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝዳንት እና የቦርድ ሊቀመንበር ጂን ሊኩን ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።

የእስያ መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ባንክ እ.አ.አ በ2016 የተቋቋመ ሲሆን ዋና ቢሮውን በቻይና ቤጂንግ አድርጓል።

ባንኩ የዓለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የባለብዝሃ ወገን ልማት ባንክ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም