ቀጥታ፡

በአፍሪካ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አካታችነት ማረጋገጥ ይገባል - የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን አካታችነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በረኦ ሀሰን ተናገሩ።   

በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ "ለአፍሪካ ዘላቂ ዕድገት ችግሮችን የሚቋቋምና አካታች መሰረተ ልማትን ማስፋፋት" በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው 8ኛው የአፍሪካ መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ሳምንት ተጠናቋል።         

አረንጓዴ ኢኮኖሚን ማሳደግ፣ ለመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥሩ ፖሊሲዎችና የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ በአፍሪካ መጻኢ ዕድል ዲጂታል መሰረተ ልማት በሚኖረው ዙሪያም ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል።     

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደኤታ አቶ በረኦ ሀሰን በሳምንቱ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ እንዳሉት፤ ሳምንቱ በአፍሪካ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የጋራ መፍትሄዎችን ማመላከት የተቻለበት ነው።    

አገራት የሚኖራቸው ትብብር በአፍሪካ መሰረተ ልማት ሥራዎችን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችሉ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።      

በአፍሪካ በመሰረተ ልማት ከመተሳሰር ጎን ለጎን ምርትና አገልግሎቶች ዝውውርን ማሳለጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና አሰራሮችን መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም የአፍሪካ አገራት ቅንጅት ወሳኝ ሚና አለው  ነው ያሉት።

በመሰረተ ልማት ዝርጋታ የበለጠ ውጤታማ ለመሆን አገራት የፈንድ አሰባሰብ አቅማቸውን ማሳደግ፣ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ፈንድ ማድረግ እንዲሁም የመንግሥትና የግል አጋርነትን ማጠናከር  ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።     

በአፍሪካ መሰረተ ልማት አቅርቦት የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ሁሉንም ዜጎች ያካተቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። 

የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማትና ኃይል ዳይሬክተር ካሙጊሻ ከዛውራ በበኩላቸው በመሰረተ ልማት ሥራዎች ውጤታማ ለመሆን ፋይናንስ አሰባሰብ ላይ ውጤታማ ስልቶችን መተግበር እንደሚገባ ገልጸዋል።   

የግል ዘርፉን ማሳተፍን ጨምሮ ዘላቂ የፋይንናንስ ምንጮችን ማፈላለግ ጊዜው የሚጠይቀው የጋራ ስራ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።   

በአፍሪካ የቴክኒክና የአቅም ውስንነቶችን መፍታት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት ልማት ኤጀንሲ -ኔፓድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ናርዶስ በቀለ በበኩላቸው ሳምንቱ አገራቱ በቀጣይ ተግባራዊ በማድረግ ለመሰረተ ልማት አቅርቦት መሻሻል አወንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሀሳቦች የተነሱበት ነው። 

ለዘላቂ ልማት የሚበጁ ልምድ ልውውጦች የተደረጉበት መሆኑን ገልጸው የአፍሪካውያን የልማት ህልሞች እውን መሆን እንደሚችሉ ያረጋገጡ ውጤቶች የተገኙበት ነው ሲሉም አብራርተዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም