ኢትዮጵያ እና ብራዚል በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ብራዚል በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 20/2017 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና ብራዚል በስኳር ኢንዱስትሪው ዘርፍ በትብብር መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ መልዕክት ሳህሉ የተመራ የልዑካን ቡድን እና በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ጋር በመሆን በብራዚል በግል የስኳር ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተሰማሩ ኩባንያዎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
ጉብኝቱ ኢትዮጵያ የስኳር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ዘመኑ ከደረሰበት የማምረት ሂደት እና ተወዳዳሪ የስኳር ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ በስኳር ተረፈ ምርቶች የሚገኙ የኢነርጂ ውጤቶችን ልምድ ለመቅሰም እና የትብብር መስኮችን መፍጠርን አላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል ።
ልዑካን ቡድኑ፣ የብራዚል የሸንኮራ እና የስኳር ኢንዱስትሪ አምራች ከሆነው የሳኦ ፓውሎ ክልል የአለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ሳሞ ቶሳቲ ጋር በቴክኖሎጂ እና የእውቀት ሽግግር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ፍሬያማ ውይይት አድርጓል።
ልዑካን ቡድኑ በቆይታው ከብራዚል ከፍተኛ የመንግስት ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈጻሚ ከሆኑ ተቋማት ጋር በዘርፉ የተቀመሩ ልምዶችን ለመቅሰም እና አብሮ ለመስራት በሚቻልባቸው መስኮች ላይ ተወያይቷል።
ብራዚል በስኳር ኢንዱስትሪው የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ደረጃ በልምድ ልውውጥ የሚደረግ ድጋፍ እንደሚቀበሉም ልዑካኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዓለም አቀፋዊ አጋርነቱን ለማስፋት፣ ከብራዚል-አፍሪካ ኢኒስቲትዩት (Brazil Africa Institute) ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ ከተቋሙ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ መግለጹን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።