ማዕከሉ ካቦዴ እና አላሞራ የተሰኙ የብርቱካናማ ስኳር ድንች ዝርያዎች አስተዋወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ማዕከሉ ካቦዴ እና አላሞራ የተሰኙ የብርቱካናማ ስኳር ድንች ዝርያዎች አስተዋወቀ

ሀዋሳ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል በምርምር ያገኛቸውን ከፍተኛ ምርት የሚሰጡና በስነ ምግብ ይዘት ተመራጭ የሆኑ ካቦዴና አላሞራ የተባሉ የብርቱካናማ ስኳር ድንች ዝርያዎች ለአካባቢው አርሶ አደሮችና ባለ ድርሻ አካላት አስተዋወቀ።
በማዕከሉ የስራ ስር ሰብሎች ተመራማሪ አቶ ዳምጠው አብወይ እንደገለጹት፤ በማዕከሉ ውጤታማነቱ ተረጋግጦ ለተጠቃሚዎች የተዋወቀው "ብርቱካናማ ስኳር ድንች" በቫይታሚን ኤ ንጥረ ነገር የበለጸገ ነው።
በምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰቱ የመቀንጨርና መሰል ችግሮችን ለማቃለል የሚያግዙ ንጥረ ነገሮችን መያዙን ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ ዝርያዎቹን በመትከል ተጠቃሚ እንዲሆን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምዕራብ አርሲ ዞን ወንዶ ወረዳ ጎቱ አኖማ ቀበሌ በ40 አርሶ አደሮች ማሳ የለማው "ብርቱካናማ ስኳር ድንች" ድርቅን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጥና ቶሎ የሚደርስ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሄክታር ከ40 ቶን በላይ ምርት መስጠት እንደሚችል ገልጸው፤ ይህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ከማገዝ አኳያ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።
"በተወሰኑ ሰብሎች ያለን እይታን በመቀየር የምግብና ስነ ምግብ ውጤት ላይ እንድናተኩር ያስችላል" ያሉት ተመራማሪው፤ አሁን ላይ ዝርያዎችን በስፋት የማሰራጨት ስራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በዕለቱም ከስኳር ድንች የተዘጋጁ የተለያዩ ምግቦች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፤ በአመራረትና ስርጭት ዙሪያ ከአርሶ አደሮችና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተደርጓል።