ቀጥታ፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ማጎልበት አስችሏል-- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ቀን  ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ማጎልበት ማስቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ገለጹ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት 19ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "አገራዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ አክብረዋል፡፡


 

የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በተለያዩ ዓለማት በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ በሚገነባ መልኩ መከበሩ ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን አብሮነትና የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት ነው፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያን ብዝሃ ማንነት እና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዓለም የሚያስተዋውቅ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የኢትዮጵያውያንን ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም የእርስ በርስ ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ ኢትዮጵያ በብዝሀ ማንነቷ የደመቀች ሆና እንድትቀጥል ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚከበረው ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች ባስመዘገበችበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የለውጡ መንግስት አሳታፊና አካታች ሥርዓት በመዘርጋት የዜጎችን የመልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ እየፈታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ችግሮችን በመደመር እሳቤ በመፍታት ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችላል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና አብሮነትን በማረጋገጥ የበለጸገች ሀገር እውን ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት የላቀ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም