ቀጥታ፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያ ደንብን አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን የወጣውን ደንብ አጸደቀ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ክፍያን ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ከህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አጽድቋል። 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ በረቂቅ ደንቡ የተደረጉ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።


 

የዳኝነት አከፋፈል ሥርዓቱን ለማዘመን፣ አጭርና ቀልጣፋ እንዲሁም ለከፋዩ ምቹ ለማድረግ ሕጉን ማውጣት እንዳስፈለገ ገልጸዋል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች እስከ አሁን ድረስ የሚጠቀሙበት የዳኝነት ገንዘብ አከፋፈል የህግ ክፍል ማስታወቂያ ደንብ በ1945 ዓ.ም የወጣ እና ማሻሻያ ሳይደረግበት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ከዚህ ባለፈ በደንቡ ያልተሸፈኑ በርካታ ጉዳዮች በመኖራቸው ወቅቱን ያገናዘበ የዳኝነት ክፍያን መወሰኛ ደንብ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ ደንቡ መውጣቱን ጨምረው ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት በቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አንስተዋል።

ደንቡ ሲሻሻል የዳኝነት አገልግሎትንም የተቀላጠፈና ፈጣን ከማድረግ አንጻር በትግበራ ወቅት ቋሚ ኮሚቴው ክትትል ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጸገነት መንግስቱ የፍትህ አገልግሎቱን በዘመናዊ አሰራር በማስደገፍ ቀልጣፋና ፈጣን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ቋሚ ኮሚቴው ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ምክር ቤቱ ደንቡ በዳኝነት ስርአቱ ላይ ያለውን ፋይዳ መርምሮ አጽድቆታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም