የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ውል ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ ውል ተፈራረመ
ድሬዳዋ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ በአስተዳደሩ ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የመሠረተ ልማት አልሚ ተቋማት እና ከፋይናንስ ሴክተሮች ጋር የሥራ የመግባቢያ ውል ተፈራርሟል።
የመግባቢያ ውሉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በተቀናጀ መንገድ ለመምራትና ለመደገፍ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማሳደግ ከቢሮው ጋር ውል ከፈረሙት መካከል የፋይናንስ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሽ ናቸው።
በስምምነቱ ስነስርዓት ላይ የተሳተፉት የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተደረጉ ዘርፈ ብዙ ድጋፎችና ክትትሎች በድሬዳዋ በአርአያነት የሚጠቀስ ውጤት ተመዝግቧል።
በንቅናቄው አስተዳደሩ እና የፌደራል መንግስት እንዲሁም የመሠረተ ልማት ተቋማትና የፋይናንስ ሴክተሮች በተቀናጀ መንገድ እያደረጉት በሚገኙት የድጋፍ ሥራዎች 31 የተዘጉና በግንባታ መጓተት ላይ የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መሸጋገራቸውን አውስተዋል።
"በተገኘው ውጤት ሳንዘናጋ ዘርፉን ለማነቃቃት የሚሰራውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን" ያሉት ከንቲባው፤ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚደረገው የተቀናጀ ድጋፍ የአስተዳደሩ ዋነኛው ትኩረት መሆኑን አረጋግጠዋል።
ዛሬ የተካሄደው የስራ ስምምነትም የተሻለ ድጋፍና ቀጣይነት ያለው ክትትል ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን በመግለፅ።
የአስተዳደሩ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር በበኩላቸው የተፈረመው የመግባቢያ ውል ከአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያስችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በመስሪያ ቦታ፣ በመለዋወጫና በፋይናንስ አቅርቦት ረገድ የሚታዩ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት መመለሳቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታቸው የተጓተቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠናቀውና ወደ ማምረት ተሸጋግረው ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ መሆናቸውን አክለዋል።
ወደ ስራ የተመለሱት ፋብሪካዎች የገበያ ዋጋን በማረጋጋት እና ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርም ለአገር ብልጽግና ጉዞ ወሳኝ አስተዋፅኦ እያደረጉ መሆናቸውን አክለዋል።
በንቅናቄው የተመዘገቡ ውጤቶችም ድሬዳዋን ባለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ በዘርፉ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ተሸላሚ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
ውሉን ከፈረሙት ተቋማት መካከል የድሬዳዋ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ከበደ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ንቅናቄውን በተሻለ ውጤት ለማጀብ ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት በቁርጠኝነት ይወጣል።
በተለይም በከንቲባው የሚመራው ወርሃዊ የስራ አፈፃፃም ግምገማ የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋማት በተናጠል እና በጋራ ተጠያቂነትን አንግበን የተጣለብንን ታላቅ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።