የኬንያው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሀሪሪ የመከላከያ ተቋማትን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
የኬንያው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሀሪሪ የመከላከያ ተቋማትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ የኬንያው ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሀሪሪ የመከላከያ ዩኒቨርሲቲን፣ ጋፋት አርማመንት ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪን፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪንና የኢፌዴሪ አየር ኃይልን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሁለቱ እህትማማች ሀገሮች ረጅም አመታትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያና ኬንያ በወታደራዊ ዲፕሎማሲ መስክ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን መግለጻቸውም እንዲሁ።
ሁለቱ ሀገራት ረጅም ድንበር እንደሚጋሩ የጠቀሱት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ ሽብርተኝነትን በመከላከል በኩል በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ጉብኝት ያደረጉባቸው የመከላከያ ኢንዱስትሪ ተቋማት የሚሰሯቸው ስራዎችም የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጥሩ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ መገንዘባቸውን መናገራቸውንም በመረጃው ተመላክቷል።
በኬንያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ቻርለስ ካሀሪሪ የተመራ ወታደራዊ ልዑክ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና ከኃይልና ከዋና መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ መወያየታቸው ይታወሳል።