ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄ ይፋ አድርጓል።

የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ህሩይ ዓሊ ንቅናቄውን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል ።

ማዕከሉ ነፃ የልብ ህክምና በመስጠት የብዙ ህፃናትን ህይወት መታደግ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ማዕከሉ አሁን ላይ በዓመት እስከ 600 ለሚደርሱ ህሙማን የቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡ 

ከዚህ ጎን ለጎን በዓመት እስከ 15 ሺህ የሚደርሱ ህሙማን የቅድመና ድህረ ቀዶ ጥገና ተመላላሽ ህክምና እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎትና የሚቀበላቸው ህሙማን ቁጥር ተመጣጣኝ አለመሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው ማዕከሉ በተለያዩ በጎ ፊቃደኞችና የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

ማዕከሉ የሚሰጠው አገልግሎት ቀጣይና ተደራሽ እንዲሆን የህብረተሰቡ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ህብረተሰቡ በዓይነትም ሆነ በገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ህክምና ለማግኘት ወረፋ የሚጠባበቁ ህጻናትን ህይወት እንዲታደግ ጠይቀዋል፡፡

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኤልዘር ኃይሌ በበኩላቸው ማዕከሉ የክትትልና የመድኃኒት አገልግሎት፣ በደም ስር ብቻ የሚሰጥ ህክምናና ሙሉ በሙሉ የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡


 

ማዕከሉ ላለፉት 35 ዓመታት ህክምና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በዚህም ከትምህርት ገበታ የቀሩ በርካታ ህጻናት ጤናቸው ተመልሶ በትምህርታቸው ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በሀገሪቱ ጥራቱን የጠበቀ የልብ ህክምና ማዕከል እንዲኖር አስቻይ ሁኔታ ከመፍጠር ጀምሮ በዘርፉ ባለሙያዎችን የማሰልጠንና አገልግሎቱን የማስፋት ስራ መሰራቱን አክለዋል፡፡

አሁን ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በዓመት እስከ 1 ሺህ 300 የሚሆኑ ህሙማን ወደ ማዕከሉ ለህክምና እንደሚላኩ ጠቅሰዋል፡፡

ማዕከሉ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ወገኖች እገዛቸውን በ6710 አጭር መልዕክት፣ የማህበሩ አባል በመሆንና ተቋሙ ድረስ በአካል በመገኘት መስጠት እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም በንቅናቄው ተቋማትን፣ ድርጅቶችንና አጋር አካላትን የማሳተፍና ተያያዥ ተግባራት እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም