በኢትዮጵያ ከፋፋይ፣ ነጣጣይ እና በታኝ የነበሩ ትርክቶችን በማረም አሰባሳቢና ገዥ ትርክት እየተገነባ ነው- ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ከፋፋይ፣ ነጣጣይ እና በታኝ የነበሩ ትርክቶችን በማረም አሰባሳቢና ገዥ ትርክት እየተገነባ ነው- ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ከፋፋይ፣ ነጣጣይ እና በታኝ የነበሩ ትርክቶችን በማረም አሰባሳቢና ገዥ ትርክት እየተገነባ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አካል የሆነ የፎቶ አውደ ርዕይ "የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም ተከፍቷል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በሁሉም መስኮች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከፋፋይ የነበረውን የፖለቲካ ስርዓት በመቀየር ብዝሃነትን ማእከል ያደረገ አካታችና የመሃል ፖለቲካ ተግባራዊ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፋፋይ፣ ነጣጣይ እና በታኝ የነበሩ ትርክቶችን በማረም በሂደት አሰባሳቢና ገዥ ትርክቶችን የመገንባት ሂደት ላይ እንገኛለን ነው ያሉት።
በኢኮኖሚው ዘርፍም ሕዝቦችን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው በተለይም በስንዴ ልማት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና ሌሎችም መስኮች ስኬት ተመዝግቧል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት የተገነቡት የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሃገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮግራሞች የቱሪዝም ሃብቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የአድዋ ድል መታሰቢያ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴቶች አስደናቂና ዘመን የማይሽራቸው የታሪክ አሻራ ሆነው በአሰባሳቢነት መቀመጣቸውን ገልጸዋል።