ደም ልገሳ ዕድሜውና ጤናው የሚፈቅድለት ሰው ሁሉ ማድረግ የሚገባው በጎ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ደም ልገሳ ዕድሜውና ጤናው የሚፈቅድለት ሰው ሁሉ ማድረግ የሚገባው በጎ ተግባር ነው

ነገሌ ቦረና ፤ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን መታደግ ዕድሜውና ጤናው የሚፈቅድለት ሰው ሁሉ ማድረግ የሚገባው በጎ ተግባር ነው ሲሉ የነጌሌ ቦረና ከተማ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ተናገሩ።
በምስራቅ ቦረና ዞን ነገሌ ቦረና ከተማ ከተለያዩ በጎ ፈቃደኞች 1 ሺህ 300 ዩኒት ደም መሰብሰቡን የከተማው ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት አስታወቀ።
ደም መለገስ ከሁሉም የሚበልጥ በጎ ተግባር መሆኑን ለበርካታ ጊዜ ደም የለገሱ ኢዜአ ያነጋገራቸው የነገሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ለአስራ ሁለት ጊዜ ደም መለገሳቸውን የተናገሩት የከተማው ነዋሪ አቶ ሰለሞን ደሳለኝ፣ በደም እጥረት ምክንያት የሰው ህይወት እንዳያልፍ በየጊዜው ደም እየለገሱ መሆኑን ተናግረዋል።
የወገኞቼን ህይወት ለማትረፍ ደም ስለግስ ዘወትር የአእምሮ እርካታና ደስታ ይሰማኛል ያሉት አቶ ሰለሞን በህይወት እስካሉ ድረስ ደም መለገስን እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።
በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ወገኖቻችንን ደም በመለገስ ልናተርፍ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ሰባት ጊዜ ደም መለገሳቸውን የተናገሩት አቶ አለማየሁ በላይ በበኩላቸው ደም በመለገሳቸው ሙሉ ጤነኛና ደስተኛ እንደሆኑ ተናግረው በየጤና ተቋማቱ በደም እጥረት የሚሰቃዩ ወገኖችን ህይወት ለመታደግ ደም መለገስ ባህል ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መስከረም በቀለ፣ ባለቤታቸውና ልጃቸውን ጨምሮ ዘጠኝ ጊዜ ደም መለገሳቸውን አንስተዋል።
ደም በመለገሴ የአንድ ሰው ህይወት በማትረፍ የሚሰማኝ ደስታና እርካታ ትልቅ ነው ያሉት ወይዘሮ መስከረም በደም እጥረት ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖችን ለማትረፍ እድሜውና ጤናው የሚፈቅድለት ሁሉ ደም መለገስ እንዳለበት መክረዋል።
የነጌሌ ቦረና ከተማ ደምና ህብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ሀላፊ አቶ ዳርጌ በርጩ ዘንድሮ በከተማው 4 ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት ከዓመታዊ እቅዱ 1 ሺህ 327 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከበጎ ፈቃደኞች በየዓመቱ የሚሰበሰበው ደም በምስራቅ ቦረና፣ ቦረና፣ በጉጂ እና በምእራብ ጉጂ ዞኖች ለ6 ሆስፒታሎች እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ከበጎ ፈቃደኞች ከተሰበሰበ 2 ሺህ 236 ዩኒት ደም ውስጥ ለነዚሁ ሆስፒታሎች 2 ሺህ 67 ዩኒት ደም መሰራጨቱን አስታውሰዋል፡፡