ቀጥታ፡

የአብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል - ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ 

ጋምቤላ፤ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦የአብሮነትንና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ። 

''ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በኑዌር ዞን ጂካዎ ወረዳ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በድምቀት ተከብሯል። 

ርዕሰ መስተዳድሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ህገ መንግስቱ ለብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያጎናፀፈውን መብት በመጠቀም የክልሉን ህዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ልንሰራ ይገባል ብለዋል። 


 

በዓሉን ስናከብርም የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነት የሚሸረሽሩ አንቅስቃሴዎች በመታገልና የህዝቦችን አንድነትና አብሮነትን በማፅናት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል። 

እንደ ክልል እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የተያዘውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አንስተዋል። 

በመሆኑም በየደረጃው የሚገኙ አካላት ህዝቡን በማስተባበር በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር የክልሉን ህዝብ  የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሯ አስገንዝበዋል። 

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኙበት ዕለት በመሆኑ ለክልሉ ህዝብ ልዩ ትርጉም አለው ብለዋል። 


 

በተለይም ህገ መንግስቱ የፀደቀበትን ዕለት በዚህ መልኩ በድምቀት ማክበራችን የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው ብለዋል።  

እለቱ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት ሲያነሱት የነበረውን የእኩልነት፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ያገኘበት ዕለት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ህገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር ረገድ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊጫወት እንደሚገባ አፈ-ጉባኤዋ አስገንዝበዋል። 

ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል ወይዘሮ ዳግማዊት ጆን በሰጡት አስተያየት በዓሉ አንዱ የሌላውን ማንነት፣ ወግና እሴት እንድናውቅ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል። 


 

በየዓመቱ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክር ነው ያለው ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጭ አቶ ኡጁሉ ኡሎከ ናቸው። 


 

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በኑዌር ዞን በጂካዎ ወረዳ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም