ቀጥታ፡

ከኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ዓሳ በማስገር ተጠቃሚ ሆነናል - ወጣቶች 

ጠምባሮ ፤ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጣምባሮ ልዩ ወረዳ ከኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ዓሳ በማስገር  በሚያገኙት ገቢ  ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ተናገሩ።

በክልሉ የዓሳ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲሁም ዓሳ የመመገብ ልምድን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገልጿል። 

የኦሞ ሰው ሰራሽ ሀይቅ የግልገል ጊቤ 3 የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ምክንያት የተፈጠረ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ሲሆን፤ ዓሳ በብዛት እየተመረተበት ይገኛል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጣምባሮ ልዩ ወረዳ ወጣቶችም ከሀይቁ ዓሳን በማስገር ህይወታቸውን እየለወጡ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።


 

ከሀይቁ ዓሳ እያሰገረ ያለው የ'ኦሞ ዓሳ አቅራቢ ማህበር' ሰብሳቢ ወጣት ደስታ ዶሾ እንዳለው፤ በአካባቢው በዓሳ ምርት ላይ መሰማራት ያልተለመደ የስራ ዘርፍ ነው።

የማህበሩ አባላት  ሰርተው ለመለወጥ ከላቸው ጽኑ ፍላጎት ዓሳ በማስገር ስራ ተሰማርተው በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት መቻላቸውንና አጠቃላይ የማህበሩ ሀብት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ መድረሱን ገልጿል።

ባገኙት ገቢም ቤተሰባቸውን ከማስተዳደር አልፈው ለሌሎች ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻላቸውን ነው የተናገረው።


 

ከማህበሩ አባላት መካከል ወጣት በረከት ክንፉና ሳሙኤል እንኮዬ፣ ዓሳ የማስገር ስራውን ከጀመሩ ወዲህ የተሻለ ገቢ እያገኙ ቤተሰባቸውን እየደገፉ ቁጠባ መጀመራቸውን ተናግረዋል።


 

የጣምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ሀብታሙ በላይነህ፤ ዓሳ በማስገር የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የግብአትና ክትትል እንዲሁም የገበያ ትስስር እየተመቻቸላቸው ይገኛል ብለዋል።

ከክልሉ ግብርና ቢሮ እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበርም ጀልባ የማቅረብ እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍ በቅርበት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሀይቁ በዓመት እስከ 6 ሺህ ቶን ዓሳ እየተመረተ መሆኑን ገልጸው የዓሳ ምርቱን የበለጠ ለማሳደግ ወደ ሀይቁ የሚያደርስ መንገድ ምቹ የማድረግ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል።


 

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሀላፊና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ ሀላፊ አቶ እያሱ ተረፈ በበኩላቸው በክልሉ የዓሳ ምርት የማሳደግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የዓሳ ዝሪያዎች ስርጭት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው በሩብ ዓመቱ ከ35 ሺህ በላይ የዓሳ ጫጩት መሰራጨቱን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመታገዝ በየአካባቢው አርሶ አደሩንና ወጣቱን በተደራጀ መልኩ በማሰማራት ውጤት እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በክልሉ በቀጥታ በማህበር የተደራጁትን ሳይጨምር ከ25 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ዓሳ በማምረት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም