በአክሱም ከተማ የአትሌቲክስ ስፖርትን ማነቃቃት ዓላማ ያደረገ የሩጫ ውድድር ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በአክሱም ከተማ የአትሌቲክስ ስፖርትን ማነቃቃት ዓላማ ያደረገ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

አክሱም፤ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ በአክሱም ከተማ የአትሌቲክስ ስፖርትን ማነቃቃት ዓላማ ያደረገ የ5 ኪሎ ሜትር ሩጫ ውድድር ተካሄደ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱም ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ፅህፈት ቤት የአትሌቲክስ ስፖርት ዋና ዳኛ መምህር ይትባረክ ተክለሃይማኖት ለኢዜአ እንደገለጹት በውድድሩ ከ15 እስከ 60 አመት የእድሜ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
ውድድሩ በከተማው ተቀዛቅዞ የቆየውን የአትሌቲክስ ስፖርት ለማነቃቃትና ተተኪዎችን ማፍራት አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በወጣት ወንድ ተወዳዳሪዎች ተኽላይ አባዲ፣አድሓኖም ዘብራአቡርክና ተስፋይ ይብራህ እንደቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሦሥተኛ ደረጃ በመያዝ የወርቅ፣የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።
በወጣት ሴቶች ብርዛፍ ታረቀ፣ደሚቃ ደስታና ሜሮን ተክለብርሃን እንደ ቅደም ተከተላቸው የወርቅ፣ ብርና ነሃስ ሜዳሊያ ተበርክቶላቸዋል።
ሳሙኤል መብራቱ፣ አዶናይ መረሳና ቃለአብ አለሙ ደግሞ በታዳጊ ህጻናት በቅደም ተከተላቸው መሰረት ከአንደኛ እስከ ሦሥተኛ በመውጣት በተመሳሳይ ተሸላሚ ሆነዋል ።
ውድድሩ በአክሱም ከተማ አስተዳደርና በተራራ ወጪዎች ወጣቶች ማህበር ትብብር የተዘጋጀ ነው።