ቀጥታ፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር እየተዘጋጀ ነው 

ጎንደር፤ ህዳር 19 ቀን 2017 (ኢዜአ)፦ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማርና ሌሎች ተግባራትን በላቀ ደረጃ ለመፈፀምና ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ወደ ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ለመሸጋገር የሚያስችለውን ዝግጅት እያከናወነ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ አስራት አጸደወይን  (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር የሚያስችለውን 13 የሚደርሱ መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን እያዘጋጀ ነው፡፡

ስራውን በተሳለጠ ሁኔታ ለማከናወንም አንድ ዐብይና 13 ንኡሳን ኮሚቴዎች በማቋቋም ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፤ ስትራቴጂክ ፕላን በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላትና ለዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ማቅረቡን ገልፀዋል፡፡

ስትራቴጂክ ፕላኑ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ህግ አውጪን፣ የተማሪዎች የመግቢያ ፖሊሲን፣የኢንዶውመንትና የሪሶርስ ሞብላይዜሽ ፖሊሲ ማቋቋሚያ አዋጅና ደንቦችን ማካተቱን ጠቁመዋል፡፡ 

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የራስ ገዝነት የሽግግር ሂደት ልምድና ተሞክሮ ለመቀመር መቻሉን ጠቁመው፤ ሂደቱ በጥሩ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የሽግግር ሂደቱን ለማገዝም የአሜሪካና የፈረንሳይ ኤምባሲዎች በዘርፉ ባለሙያዎች የታገዘ የስልጠናና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ድጋፍ እየሰጡን እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ መብቶች የአካዳሚክና የአስተዳደር ነጻነትን እንደሚያጎናጽፍ ጠቁመው፤ መምህራንና ሰራተኞች እንደ አስተዋጽአቸውና ተሳትፏቸው ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ምቹ የኢኮኖሚ አውድ የሚፈጥር መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በዝግጅት ምዕራፉ ምርምርን፣ የማህበረሰብ አገልግሎትንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳደግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀብት በማመንጨት የገቢ አቅሙን ማሳደግ የሚያስችሉትን ተግባራት መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡  

ሀብት የስራ እድልና ገቢን የሚፈጥሩ ዘጠኝ የሚሆኑ ተቋማትና የስራ ዘርፎች በጥናት መለየታቸውን ጠቁመው፤ በቅርቡም ሞዴል ፋርማሲ በመክፈት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የመድሃኒት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ፕሬዚዳንቱ አስራት (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

በቀጣዩ ዓመት ወደ ራስ ገዝነት ከሚሸጋገሩ የአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፤  ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዩንቨርሲቲው በመደበኛው፣ በኤክስቴሽንና በክረምት መርሃ ግብር ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ለማወቅት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም