ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎችን ያስተናገደው ንግድ ባንክ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በሰባት ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈትን አስተናግዶ በቀሪዎቹ ሶስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

ቡድኑ ሰባት ጎሎችን ሲያስቆጥር ያስተናገደው አንድ ግብ ብቻ ነው።

በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በ12 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። 

የዘጠነኛ ሳምንት የሊጉ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማን ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ያገናኛል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ካደረጋቸው ስምንት ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት በማስተናገድ አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ግቦችን ሲያስቆጥር ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ የሚመራው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ13 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ እስከ አሁን በሊጉ ባደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሶስቱን ሲያሸንፍ በሁለቱ ተሸንፎ በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

በሰባቱ ጨዋታዎች 11 ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎችን አስተናግዷል።

በይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በ11 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ 10 ሰዓት፣ አርባምንጭ ከተማ ከመቻል ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የዘጠነኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።

መቻል በ14 ነጥብ ሊጉን እየመራ ሲገኝ በተመሳሳይ 14 ነጥብ ያለው ወላይታ ድቻ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

የዘጠነኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የመቀሌ 70 እንደርታው አጥቂ ያሬድ ብርሃኑ በአምስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመራ ይገኛል።

ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ቻርልስ ሙሲጌ እና ሌላኛው የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊ መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራና የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ በተመሳሳይ አራት ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም