ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች በተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ላይ ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች በተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ ላይ ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይ ኤም ኤፍ) የተራዘመ የብድር አቅርቦት ማዕቀፍ (ኤክስቴንድድ ክሬዲት ፋሲሊቲ) ሁለተኛ ግምገማ ላይ በባለሙያዎች ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚለቀቅ ተገልጿል።
የተራዘመ የብድር አቅርቦቱ ለአራት ዓመት የሚቆየው የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ማዕቀፍ መሆኑን አይ ኤም ኤፍ ገልጿል።
መርሃ ግብሩ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም መጽደቁ ይታወቃል።
በአልቫሮ ፒሪስ የተመራ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ከሕዳር 3 እስከ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ቆይታ አድርጓል።
ቡድኑ በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የተራዘመ የብድር አቅርቦት ሁለተኛ ግምገማ አማካኝነት ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፕሮግራም እያደረገ ያለው ድጋፍ አፈጻጸምና የኢትዮጵያ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አስመልክቶ ውይይት አድርጓል።
አልቫሮ ፒሪስ ቡድኑ በኢትዮጵያ የነበረውን ተልዕኮ አስመልክቶ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአይ ኤም ኤፍ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከገንዘብ ሚኒስትትር አሕመድ ሽዴ፣ ከገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ እና ከሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።
ባለሙያዎቹ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባንኮችና የንግድ ተቋማት ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በገበያ ወደ ሚወሰን የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ያደረገችው ሽግግርን ጨምሮ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ በመደበኛ እና የትይዩ ገበያዎች መካከል ያለውን ልዩነት ከ10 በመቶ በታች እንዳወረደው ነው የቡድኑ መሪ የገለጹት።
የአይ ኤም ኤፍ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ በባለሙያዎች ደረጃ የተደረሰውን ስምምነት በቀጣይ ሳምንታት እንደሚገመግም ገልጸዋል።
የቦርዱ ግምገማ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ 251 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገንዘብ እንደሚለቀቅም ጠቁመዋል።
ቀጣይ የተራዘመ የብድር አቅርቦት ግምገማዎች በየስድስት ወሩ እንደሚካሄዱ ፒሪስ መግለጻቸውን የአይ ኤም ኤፍ የፕሬስ መግለጫ ያመለክታል።
የስራ አስፈጻሚ ቦርዱ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተባለውን መርሐ-ግብር ሐምሌ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ሲያጸድቅ ወዲያውኑ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግሥት መልቀቁ የሚታወስ ነው።