የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና አገልግሎት(WAM) ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና አገልግሎት(WAM) ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር ስምምነት ተፈራረመ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና አገልግሎት ኤምሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ(WAM) ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን የትብብር ስምምነት በአቡ ዳቢ ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና አገልግሎት(WAM) የዜና ዘርፍ ዳይሬክተር ጀማል ናስር አል ሱዋይደር ፈርመውታል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ኡመር ሁሴን(ዶ/ር)፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሚዲያ ቢሮ ዳይሬክተር ጀነራል(NMO) እና የኤምሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጀነራል ጀማል መሐመድ አል ካቢ(ዶ/ር) እንዲሁም ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች ተገኝተዋል።
ስምምነቱ የተደረገው በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እየተካሄደ ካለው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ኮንግረንስ(GMC 2024) ጎን ለጎን ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዜና አገልግሎቶቹ መካከል የተፈረመው የትብብር ስምምነት ዘላቂ ልማትን የሚደግፉ የሚዲያ ይዘቶችን ለማቅረብና ዓለም አቀፍ የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት ያስችላል።
በተጨማሪም በተቋማቱ መካከል ያለውን የዜናና የሚዲያ ይዘት ልውውጥን በማሳለጥ ጠንካራ የሚዲያ ትብብርን ለመፍጠርና በዚህም ህጎችንና ደንቦችን ባከበረ መልኩ የጋራ አላማዎችን ማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
ስምምነቱ ተቋማቱ በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዘላቂ ልማትን የሚደግፉ ፋይዳ ያላቸውን የሚዲያ ይዘቶች ለማቅረብ እና የሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪነትን በማሳደግ ዓለም አቀፍ ስኬቶችን በመረጃ ተደራሽ ለማድረግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በስምምነቱ አማካኝነት ተቋማቱ ዕለታዊ ዜና፣ ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመለዋወጥ ባላቸው የሚዲያ አማራጮችና ሌሎች አጋሮቻቸው እንዲያሰራጩትና እንዲጠቀሙበት ያደርጋሉ።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የዜና አገልግሎት(WAM) የዜና ዘርፍ ዳይሬክተር ጃማል ናስር አል ሱዋይደር በበኩላቸው ስምምነቱ የኤምሬትስ ኒውስ ኤጀንሲ ግንባር ቀደም ከሆኑ ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ጋር ያለውን አጋርነቶች ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያመላክት ገልጸዋል።
ተቋሙ በትብብር የጋራ የሚዲያ ተልዕኮዎችን ማሳካት የሚያስችል ዘላቂ የመገናኛ ብዙሃን ሞዴል አማራጭ ማቅረቡንም አመልክተዋል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እየተካሄደ ያለው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የሚዲያ ኮንግረንስ ነገ እንደሚጠናቀቅ ከኤምሬትስ የዜና አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።