ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሞሮኮ ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማስፋት ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ሞሮኮ በቁልፍ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማስፋት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በሞሮኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ናርዶስ አያሌው ከሞሮኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምስራቅና ምዕራብ አፍሪካ ዘርፍ ኃላፊ መሐመድ ኢላሉዊ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ሁለቱ እህትማማች አገራት ስላላቸው ታሪካዊና የወዳጅነት ግንኙነት ተነስቷል።

ሁለቱ ወገኖች በውይይታቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ትምህርትና ስልጠና፣ ባህል እና ቱሪዝምን ጨምሮ በተለያዩ ቁልፍ መስኮች ያላቸውን ግንኙነት ለማስፋት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በሁለቱ ታሪካዊ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣውን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ መግለጻቸውን በሞሮኮ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም