ቀጥታ፡

በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሊባኖስ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተደረገ ባለው ጥረት ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ቤይሩት ከሚገኘው ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ዲፕሎማቶች እና ሠራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል።


 

በውይይቱ ፥ወደ አገራቸው ለመመለስ በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ በኩል የተመዘገቡ ዜጎችን በፍጥነት ወደ አገራቸው የመመለሱ ሥራ ወቅታዊ ሁኔታውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አሳስበዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀኔራል ጽህፈት ቤት የሚሰሩ ዲፕሎማቶችን እና ሠራተኞችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እየተወጡት ላለው አገራዊ ግዴታ አኩሪ ተግባር መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም