በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው- ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል አስተማማኝ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የደጀን ወረዳ አርሶ አደሮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት፣ በህይወት የመኖር ዋስትናችን ነው ይላሉ።
በወረዳው የጢቅ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መኩሪያው ታደለ፤ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ሰላም መሆኑን ተናግረዋል።
የሰላም ጉዳይ የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን አንስተው፥ በተለይም ለአርሶ አደር የእርሻና የግብርና ስራ የሰላም ዋጋው ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በወረዳው የዘመትን ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሸጋው ከፍያለው በበኩላቸው፦ ሰላም ከምንም ነገር በፊት ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
"የሰላም እጦት ቤተሰብንና ሀገርን ይጎዳል" ያሉት አርሶ አደሩ የሚኖሩበት አካባቢ ሰላም በመሆኑ የግብርና ስራቸውን በአግባቡ ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይነትም ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ በግጭት ውስጥ የሚገኙ ሁሉ በንግግር የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
የምስራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፤ በዞኑ የሰላም ማስከበርና የልማት ስራዎች ጎን ለጎን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም አብዛኛዎቹ ወረዳዎች ወደ ሰላምና መረጋጋት በመመለሳቸው መደበኛ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ፤ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው የተሻለ የሰላም ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣የክልሉ የፀጥታ ኃይል፣ የፖለቲካ አመራሩና ህዝቡ ባደረጉት ርብርብ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ የተሻለ ሰላም በመኖሩ የግብርና ልማትና ሌሎችም ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በጫካ የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም በሰላም እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፥ አንጻራዊ ሰላምን ወደ አስተማማኝ ሁኔታ ለማሸጋገር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
አመራሩ ለዘላቂ ሰላምና ልማት በግንባር ቀደምነት መሰለፍ እንዳለበት የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ህዝቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍም የማስተባበር ሚናውን ይወጣል ብለዋል።
መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች ሁልጊዜም በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸው፥ በጫካ የሚገኙ የታጠቁ ወገኖችም ፍላጎታቸውንና ሀሳቦቻቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረብ ከመንግስት ጋር እንዲወያዩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም ሁሉም ተባብሮ ክልሉንና ሀገርን ወደ ከፍታ የሚወስድ ስራ መስራት ላይ ማተኮር ይኖርበታል ብለዋል።