የአፍሪካ ሀገራት በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ያላቸውን አቅም ለማጎልበት በትብብር ሊሰሩ ይገባል - ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ሀገራት በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ያላቸውን አቅም ለማጎልበት በትብብር ሊሰሩ ይገባል - ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት በአቪዬሽን ቴክኖሎጂ ያላቸውን አቅም ለማጎልበት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም የሀገራቱ አየር ኃይል አዛዦች በተገኙበት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ግቢ ዛሬ ተካሂዷል።
ኢትዮጵያ ከ89 ዓመታት በፊት የአየር ኃይል ቴክኖሎጂ ስትታጠቅ በአፍሪካ ቀርቶ በኤዢያም ቀዳሚ እንደነበረች የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ይናገራሉ።
አየር ኃይል በማሰልጠንና በውጊያ አቅሙ ትልቅ ከፍታ እንደነበረው አስታውሰው፤ ተቋሙ በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ በማለፉ የዕድሜውን ያህል እንዳላደገ ገልፀዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በዚህ ቁጭት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በመሥራት ተቋሙ በፈጣን እመርታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ከሰው ኃይል ማብቃት እስከ አየር ክልል ጥበቃ ትልቅ ውለታ መዋሏን ገልጸዋል።
ዛሬም በፓን አፍሪካዊነት መንፈስ የቀደመ ሚናዋን በማጠናከር፣ አፍሪካ በአቪየሽን ዘርፍ የጋራ ቋንቋ እንዲኖራት የሚያስችል ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ የአፍሪካ አየር ኃይሎች ማህበር በማቋቋም በየጊዜም የሚመክርና የሚዘክር አደረጃጀት ለማቋቋም የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም መካሄዱም በትብብርና በተሞክሮ ልውውጥ የተሻለ አቅም ለመገንባት በማለም እንደሆነ ነው ያነሱት።
ዓለም በአቪየሽን ቴክኖሎጂ የረቀቀና የላቀ ደረጃ ላይ መድረሱን በማስታወስ፣ የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን የተሻለ ነገር በመጋራት በዘርፉ ራስን ማብቃት እንደሚገባ አንስተዋል።
ሀገራት የራሳቸውን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከቴክኖሎጂ ቅኝ ግዛት መላቀቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በመጠበቅ የነበረውን ታሪካዊ ሚና አስታውሰዋል።
ባለፉት ዓመታት በጥናት ላይ በመመርኮዝ ቴክኖሎጂ በሚሸከም የሰው ኃይል፤ በዘመናዊ ትጥቅ፣ በውጊያ መሰረተ ልማት እንዲሁም አየር ኃይሉ ለሁሉም መስክ ምሳሌ የሆነ ተቋም በሚያደርጉ ሥራዎች ላይ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል።
በዚህም ባለንበት ቀጣና ማንኛውም ጥቃት መመከት የሚያስችል ብቁ አየር ኃይል ተቋም ተገንብቷል ነው ያሉት።