የክልሉን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ ነው
አርባምንጭ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ኢንዱስትሪዎች ምርታማና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችል የምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።
የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ቦጋለ ቦሼ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አቅማቸውን የማጠናከርና የማብቃት ስራ እየተሰራ ነው።
ኢንዱስትሪዎቹ ያሉባቸውን ወቅታዊ ችግር መሠረት በማድረግ የማሽን፣ የፋይናንስ፣ የግብአት አቅርቦት፣ የክህሎት እና የገበያ ትስስር በመፍጠር በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተቀናጀ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ብርሃኑ በበኩላቸው በክልሉ ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ዛሬም ከጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ኮፕሬሽን ጋር በመሆን በክልሉ በአርባምንጭና ዲላ ክላስተሮች ለተመረጡ 10 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የተለያዩ ማሽኖች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በአንድ ዓመት ውስጥ ከ150 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
የተደረገላቸው የማሽነሪ ድጋፍ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ከመጨመር ባለፈ በሀገር ውስጥና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።
የማሽነሪ ድጋፍ ካገኙት መካከል በአርባምንጭ ከተማ በወተት ምርት ማቀነባበር ላይ የተሰማራው 'ያላ አግሮ ኢንዱስትሪ' ፋብሪካ ባለቤት አቶ ኤፍሬም እስራኤል ባገኙት ድጋፍ ጥራት ያለው ወተት ለማቅረብ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የፋብሪካው በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ሲገባ በቀን ከ24 ሺህ ሊትር በላይ ወተት እንደሚያመርት ጠቁመዋል።
ከተመሠረተ አንድ ዓመት ከስምንት ወር ውስጥ ለ22 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረው በዲላ ከተማ የሚገኘው የ'ሌሎ ዳቦ' ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤሊያስ ይልማ፤ ፋብሪካው ዲላ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ለተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ዳቦ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
ስራ አስኪያጁ አክለው የተሰጠው የማሽን ድጋፍ የበለጠ ምርታማ እንዲሆ ያስችለናል ብለዋል።
በመድረኩም የዘርፉ ከፍተኛ አመራር አባላትና ባለሙያዎች እንዲሁም በአርባምንጭና ዲላ ከተሞች የሚገኙ መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ተሳትፈዋል።