ብልፅግና ፓርቲ ያለፈውን የአግላይነት ስርዓት አስቀርቶ እኩልነትን አስፍኗል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ ያለፈውን የአግላይነት ስርዓት አስቀርቶ እኩልነትን አስፍኗል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ሰመራ ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ የብልፅግና ፓርቲ ያለፈውን የአግላይነት ስርዓት አስቀርቶ እኩልነትን ያስፈነ መሆኑን የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።
"የሀሳብ ልዕልና፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የብልፅግና ፓርቲ 5ተኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ መርሃ ግብር በክልል ደረጃ ዛሬ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር አወል በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ሰፍነው የቆዩትን የአግላይነት ስርዓትን በማስቀረት እኩልነትንና አካታችነትን በተግባር ያሳየና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው።
ክልሉም በፓርቲው ውስጥ ባለው እኩል ተሳትፎ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን እያጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ፓርቲው በጠንካራ አመራር በመመራት የጋራ የሆኑ ለውጦችን ለማሳካት መቻሉንም ገልጸዋል።
ፓርቲው በሂደት የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል ቁርጠኝነት ያለውና አመራር አባላቱም ይህንን ሚና እየተወጡ መምጣታቸውን አስታውቀዋል።
በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ "ብልፅግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ስራዎች እንዲሰሩና ለውጦች እንዲመጡ አድርጓል" ብለዋል።
ፓርቲው ባለፉት ዓመታት ኑሯቸውን በውጭ ያደረጉ ወገኖች ወደ አገር እንዲገቡ እና በልማት እንዲሳተፉ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ከክልል፣ ዞንና ወረዳ የተውጣጡ አመራር አባላት በተገኙበት የማጠቃለያው መርሃ ግብር ተካሂዷል።