ቀጥታ፡

በነዳጅ ስርጭት ላይ ህገ ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ይወሰዳል - ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ

ባህር ዳር፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በነዳጅ ስርጭት ላይ ህገ ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መግለጫ ለጋዜጠኞች ሰጥቷል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ በመግለጫው እንደገለጹት፤ ነዳጅ በመንግስት የዋጋ ትመና በፍትሃዊነት ለተጠቃሚዎች ከሚሰራጩ ምርቶች አንዱ ነው።

በዚህም በናፍጣ፣ ቤንዚልና ነጭ ጋዝ ላይ የአቅርቦት ስርጭትን ፍትሃዊነት ለማስፈን ግብይቱ በዲጅታል እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።

በናፍጣና ነጭ ጋዝ ላይ የአቅርቦት እጥረት ችግር ባለመኖሩ ስርጭቱም መንግስት ባስቀመጠው የአሰራር አቅጣጫ በአግባቡ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቤንዚል ላይ የአቅርቦት ችግር በመኖሩ ለሚመለከታቸው ተሽከርካሪዎች በፍትሃዊነት የማሰራጨት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። 

በዚህም የመንግስት ተሽከርካሪዎች፣ የግል አውቶሞቢሎች፣ አየር መንገድ የሚሰሩ ታክሲዎችና ዳማሶች በሳምንት አንድ ጊዜ በታንከራቸው ልክ በመሙላት እንዲሰሩ የተቀመጠውን አሰራር ማክበር እንዳለባቸው  አስገንዘበዋል።

በመስኖ ልማት የተሰማሩ የተፈቀደላቸው አርሶ አደሮችም የተፈቀደላቸውን ቤንዚን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አላስፈላጊ ጥያቄ በተደጋጋሚ በመጠየቅ፣ በተለምዶ ዳማስ በመባል የምትጠራው ተሽከርካሪ ላይ ተጨማሪ ታንከር በማሰራት ነዳጅ በህገ ወጦች እጅ እንዲገባ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ችግሩን ለመፍታት ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በተደረገ ቁጥጥር ከ135 ሺህ 500 ሊትር በላይ ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ተከዝኖና ሲጓጓዝ ተይዞ መወረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በተለይ የነዳጅ ማደያ ባለባቸው ከተሞችና አካባቢዎች 20 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ በጀሪካ፣ በርሚልና ሌሎች መያዣዎች ይዞ የሚገኝ ከሆነ ሙሉ በሙሉ እንደሚወረስ አስረድተዋል።

ይህ እርምጃም የነዳጅ ችርቻሮ ፈቃድ ያላቸውም ቢሆኑም በህግ ከተፈቀደላቸው ውጪ ይዘው ከተገኙ ነዳጅ ተወርሶ ፈቃዳቸው የሚመክን መሆኑን አውቀው ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በነዳጅ ማደያዎች የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ የተመደቡ የጸጥታ አካላት፣ የማደያ ባለቤቶችም ካልተገባ ጥቅም ራሳቸውን በመጠበቅ መንግስት ላስቀመጠው አሰራር ተገዥ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም