ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማፅናት የጀመርነውን ተስፋ ሰጪ የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ እንረባረባለን - አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን - ኢዜአ አማርኛ
ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማፅናት የጀመርነውን ተስፋ ሰጪ የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ እንረባረባለን - አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን
ድሬዳዋ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ህብረ ብሔራዊ አንድነትና እኩልነትን በማፅናት የተጀመሩ የብልጽግና ትልሞችን ከዳር ለማድረስ ርብርቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን ተናገሩ።
በድሬዳዋ አስተዳደር የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የማጠቃለያ በዓል ዛሬ በውይይት ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል በአስተዳደሩ ከህዳር 03 ቀን 2017ዓ.ም ጀምሮ በልማት ስራዎች፣ በደም ልገሳ፣ በፌደራሊዝም ስርዓት ግንባታ እና በህገ መንግስቱ ፅንሰ ሃሳቦች ግንዛቤ ማጎልበቻ ውይይቶች እና በመሰል መርሃ ግብሮች ሲከበር ቆይቷል።
የበዓሉ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ "ሀገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሐሳብ በፌደራሊዝም ፅንሰ ሐሳብና በህገ መንግስቱ ትሩፋቶች ላይ በውይይት ተከብሯል።
በውይይቱ ላይ የአስተዳደሩ ምክርቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ እንደተናገሩት፤ በዓሉ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ያላቸውን ማንነት፣ ባህል፣ ወግ እና ታሪክ በአደባባይ በማውጣትና በአንድነት የሚያከብሩት መድረክ ነው።
በተለይም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከበሩት በዓላት የርስ በርስ አንድነትና የወል ማንነቶችንና ትርክቶችን በማፅናት፣ አገራዊ ገፅታን በመገንባት ረገድ የተሻለ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ይበልጥ በማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የተገኙ የብልፅግና ግቦችን ለማሳካት ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በበዓሉ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በዓሉ አገራዊ የብልፅግና ትልሞችን ለማሳካት እና ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የጀመርናቸውን ስራዎች ይበልጥ አፅንተን ለማስቀጠል የጋራ መግባባት የተፈጠረበት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ በህገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ስራዎችን የበለጠ እንዲረዳና አብሮነትና ወንድማማችነት ይበልጥ እንዲጎለብት እያስቻለ መሆኑን በማስታወስ።
ይህን ህብረ ብሔራዊ አንድነት በመጠበቅ የሚገጥሙንን ወቅታዊ ፈተናዎች በአንድነት በመሻገር ብዝሃነትና እኩልነትን አክብረን ህዝባችንን ከድህነት በማላቀቅ የተሻለች ድሬዳዋን ለመገንባት እንረባረባለን ብለዋል።
በማጠቃለያው በዓል የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የማህበረሰብ ባህላዊ መሪዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ተሳትፈዋል።
እንዲሁም የአዲስ አበባ ምክር ቤት፣ የኦሮሚያ፣ የሐረሪ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችና ምክትል አፈ ጉባኤዎችም በበዓሉ ተሳታፊ ሆነዋል።