ቀጥታ፡

ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ለመከላከል ድንበር ዘለል ትብብርን ለማጠናከር እየተሰራ ነው 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ለመከላከል ድንበር ዘለል ትብብርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ። 

ትኩረት በሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ድንበር ተሻጋሪ ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። 

በጤና ሚኒስቴር አማካሪ የሆኑት ሌሊሳ አማኑኤል እንደገለጹት፤ ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት የኅብረተሰብ የጤና ችግር ነው።

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ እነዚህ በሽታዎችን ለመከላከል ትኩረት አድርጋ እየሰራች ባለው ሥራ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እነዚህ በሽታዎች በሰውና በእንስሳት ዝውውር የሚተላለፉ በመሆናቸው ድንበር ከሚጋሩ አገራት ጋር በትብብር መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

የውይይት መድረኩም ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር ከሚጋሩ አገራት ጋር እየተደረገ ያለና በሽታዎቹን በትብብር ለማጥፋት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል። 


 

በዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ዶክተር ኖንሕላንሕላ ዲላሚኒ በበኩላቸው የሰዎችና የእንስሳት ዝውውር ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎችን ሥርጭት የሚያስፋፋ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከበርካታ አገራት ጋር ድንበር የምትጋራ አገር መሆኗ እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል  ለምታደርገው ጥረት ፈተና መሆኑን ጠቁመው ውይይቱ በጋራ ትብብርና ጥረት በሽታዎቹን ለማጥፋተ የሚያግዝ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን፣ በኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ድንበር ላይ እነዚህን በሽታዎች በመከላከል በኩል እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።  

ውይይቱ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳትፈዋል። 

 

 

     

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም