ቀጥታ፡

''ኪፕ ክላውድ'' የተሰኘ የፈረንሳይ ኩባንያ በኢትዮጵያ የምግብ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ''ኪፕ ክላውድ'' የተሰኘው የፈረንሳይ ኩባንያ በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት፣ በፈረንሳይ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማስተባበር በኢትዮጵያ ሊቋቋም በሂደት ላይ የሚገኘውን ''ኪፕ ክላውድ'' የምግብ ማቀነባበሪያ በተመለከተ የኩባንያው የስራ ሀላፊዎች መግለጫ ሰጥተዋል።

የኪፕ ክላውድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሰበስቲያን ድላሞት፤ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመረዳት በዘርፉ ለመሰማራት መምጣታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረትና ምቹ ሁኔታ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ ግብዓቶቹን ለደንበኞቹ ከድርጅቱ በብዛት ለመረከብ ፍላጎት በማሳየቱም ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በፈረንሳይ ታዋቂ የሆነውን የኪፕ ክላውድ የምግብ ማቀነባበሪያ ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ በዝግጅት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በፋብሪካው ለሚመረቱ ምግቦች ግብዓቱን ከዚሁ የሚጠቀሙ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የኪፕ ክላውድ ኤክስፖርትና ንግድ ዘርፍ ዳይሬክተር ራሄል ሳህሉ፤ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ልማት የመግባት የረጅም ጊዜ እቅድና ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጸው አሁን ላይ እውን እየሆነ ነው ብለዋል።

ሌላኛው የድርጅቱ አጋር ሚካኤል ደምሰው፤ የስራ ሂደቶችን አልፎ ፋብሪካው ወደ ማምረት ሲገባ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር የላቀ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከድርጅቱ የምግብ አቅርቦት ስለሚፈልግ ምርቱን ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ማቅረብ የሚያስችለን ይሆናል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዘርፍ የሰጠችው ትኩረት በቀጣይ ከዓለም ሀገራት ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዷ እንደሚያደርጋት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር መሳብ የተቻለ ሲሆን በ2017 በጀት አመት ደግሞ 4 ነጥብ 52 ቢሊዮን ዶላር ለመሳብ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም