የክልሉ ህዝብ በብዝሃነቱ ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ ልንቆም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ህዝብ በብዝሃነቱ ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ ልንቆም ይገባል
ጋምቤላ፤ ህዳር 18/2017 (ኢዜአ)፦ የክልሉ ህዝብ በብዝሃነቱ ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
''ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሐሳብ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በጋምቤላ ክልል ደረጃ በኑዌር ዞን ጂካዎ ወረዳ ዛሬ በሲምፖዚየም መከበር ጀምሯል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የክልሉ ህዝብ ህገ-መንግስቱ ያጎናፀፈውን መብት ተጠቅሞ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፎች ያለውን ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያጎለበተ መጥቷል።
ክልሉ በበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች የበለፀገ ይሁን እንጂ እነዚህን ፀጋዎች በአግባቡ አልምቶ ከመጠቀም አንፃር ውስንነቶች እንዳሉት የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሯ፤ በመሆኑም በብዝሃነቱ ውስጥ ያለውን አንድነት በማጠናከር ለክልሉ ሁለንተናዊ ዕድገት በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል ።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ በበኩላቸው በዓሉ እንደ ሀገር መከበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ መልካም ግንኙነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እያደረገ ነው ብለዋል።
በተለይም በብዝሃነት ውስጥ ያለውን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር ረገድ የበዓሉ መከበር ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ጋምቤላ በርካታ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተፈቃቅረው በጋራ የሚኖሩበት አካባቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓሉ ይህን መስተጋብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
ሀገራዊ መግባባትንና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ የተዛባ ትርክትን ለማስተካከልና ብዝሃነትን በአግባቡ ለማስተናገድ በዓሉ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
አፈ ጉባዔዋ አክለውም የፌደራል ስርዓቱ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ባለፈ አንዱ የሌላውን ባህልና እሴት እንዲረዳ በር የከፈተ በመሆኑ ዕለቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል።
በሲምፖዚየሙ ላይ ''ህብረ ብሔራዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ተግዳሮቶችና የመፍትሔ ሀሳቦች'' በሚል ርዕስ ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ከኦሮሚያ ክልል ከመጡ አባ ገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎችም በመድረኩ ተሳትፈዋል።
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በክልሉ ደረጃ ነገም ቀጥሎ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት እንደሚከበር ተመላክቷል።