ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ ገለጸች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ጣሊያን የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር መሆኗን በተለይም በልማት ትብብር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ የምታደርገውን ጠንካራ ተሳትፎ ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ እና እንደምታመሠግን ተናግረዋል።
በመሪዎች ደረጃ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ የገለጹት አምባሳደር ምስጋኑ፤ በሚኒስትር ዴኤታው እየተካሄደ ያለው ጉብኝትም የሁለቱን ሀገራት የትብብር አድማስ ለማስፋት እና አዳዲስ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ጣሊያን በአፍሪካ የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማጠናከር ያወጣችው የማቴ ዕቅድ(Mattei Plan) የኢትዮጵያም የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ከመጥቀሙ ባሻገር ለሌሎችም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ ገልጸዋል።
የጣሊያን የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ጆርጂኦ ሲሊ በበኩላቸው፤ በመንግሥታቸው ኢትዮጵያ ትኩረት የሚሰጣት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር ማስፋት እንደምትፈልግም ጠቅሰዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዎቹ በውይይታቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የልማት ትብብር ስምምነት በአዲስ መንፈስ መቃኘት እንደሚያስፈልግ መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።