በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤት አመራር አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤት አመራር አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ
ሆሳዕና ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ):- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት እንዲጠናከሩ የትምህርት ቤት አመራር አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
በክልሉ "የትምህርት ቤት አመራር ብቃት ለላቀ የትምህርት ጥራት" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ የትምህርት ቤት አመራር አባላት ስልጠና በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ተጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን አሳታፊ በሆነ መልኩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
እነዚህን ተግባራት ከግብ ለማድረስና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የትምህርት አመራሩን አቅም ማጎልበትና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተው ክልሉ በዚህ ላይ አበክሮ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም መሻሻሎች መምጣታቸውን ጠቅሰው ይህ በዘላቂነት እንዲቀጥል በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎች እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
በተለይም የትምህርት ግብአት ማሟላት፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ለመምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናና የትምህርት አመራሩን ማብቃት በተከታታይነት ይከናወናል ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፣ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው የትምህርት አመራር ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም በጥናት ላይ የተመሰረተና የተሻሉ ተሞክሮዎች የተካተቱበት የሪፎርም ስራ መሰራቱን ያነሱት አቶ አንተነህ በዚህም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ የትምህርት አመራር ምደባ ተሰጥቶ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ያለፉና ለስልጠና የመጡ የትምህርት ቤት አመራር አባላት ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለያዩ ርዕሶች ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው ስልጠና ማስጀመሪያ ላይ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።